የሀገርን ሕልውና የሚያጸኑ ባህሎች፣ እሴቶችና ትውፊቶች የሚገነቡ ተቋማት ለኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ሕልውና የሚያጸኑ ባህሎች፣ እሴቶችና ትውፊቶች የሚገነቡ ተቋማት ለኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ):-በሀገር ግንባታ ሂደት ከመሠረተ-ልማት ጎን ለጎን የሀገርን ሕልውና የሚያጸኑ ባህሎች፣ እሴቶችና ትውፊቶች የሚገነቡ ተቋማት ለኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ በኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ የሚከተላቸው ሃይማኖቶች መሠረታዊ አስተምህሮት የተቀራረበና ሰላምን የሚሰብክ መሆኑን ጠቁመዋል።
በታሪክ ሂደት ውስጥ በኢትዮጵያ እምነቶች መካከል ከፍተኛ የሰላምና የትብብር ዘመናት በስፋት መታየታቸውን አውስተው፤ ክርስትናም ሆነ እስልምና የሰላም እምነቶች ስለመሆናቸው ትልቁና ሕያው ማረጋገጫ ኢትዮጵያ መሆኗን አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ገንዘብ አዋጥተውና አግዘው ለክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን እንደሚሠሩ፤ በተመሳሳይ መልኩም ክርስቲያኖች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ ለሙስሊሞች መስጊድ እንደሚገነቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ ይህም የአገሪቷ እውነተኛ የታሪክ መሠረት መሆኑን አብራርተዋል።
አገራዊ ምርጫውን ለማደናቀፍ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ቦምቦችና ክላሽንኮቮችን በመያዝ ሰፊ የነውጥ ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰው፤ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ጥንካሬ ሴራው ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳርና በጎንደር ቦምብ ለመጣልና ከፍተኛ ሁከት ለመፍጠር ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰው፤ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማሰናከል ታስቦ የተደረገ እንደነበር አመልክተዋል።
በምርጫ ጣቢያዎች ላይ በነበረው ከፍተኛ ጥንቃቄ ምክንያት ዓላማቸው የከሸፈባቸው አጥፊ ኃይሎች፣ ሕዝቡን ለማጥቃት በአርሲ ወደ ሚገኝ አንድ መንደር ማቅናታቸውን ጠቅሰዋል።
በዚያም መንደር ሕዝብን ከጥቃት የሚከላከል ሃይል እና ሕዝብን የሚያጠቃ ኃይል መጋጨታቸውን አመልክተው፤ በወቅቱ በተከሰተው ግጭት የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል።
ሕይወታቸው ካለፉት 11 ሰዎች መካከል ስምንቱ ሕዝባቸው እንዳይገደል የተፋለሙ የሚሊሻና የፖሊስ አባላት መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ እነዚህ ስምንት የፀጥታ አባላት ሕዝባቸው እንዳይገደል ተፋልመው፣ ሕይወታቸውን ገብረው የብዙ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት የታደጉ ናቸው፤ በመሆኑም ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
ነገር ግን በርካታ ፖለቲከኞች ለእኛ ሲሉ የሞቱትን የፀጥታ አባላት ከማወደስና ከማመስገን ይልቅ፣ መስዋዕትነታቸውን ለማራከስና ችግሩን የእምነትና የብሔር መልክ ለመስጠት መሞከራቸውን ጠቅሰው፤ የዚህ ዓይነቱ ተግባር እጅግ አሳፋሪ እንደነበር ገልጸዋል።
በወቅቱ የተከሰተው ግጭት የእምነት ሳይሆን ሽፍቶች ሰው በመግደልና በማፈናቀል ሰላማዊ ድባብ ለማጥልሸትና ሰላም ለማደፍረስ ያደረጉት ሙከራ መሆኑን ገልጸው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለእነዚህ ውድ የፀጥታ አባላት ተገቢውን ዕውቅናና ክብር እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በአርሲው ግጭት ዙሪያ እስካሁን 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ ጥላ ሥር እንደሚገኙ አመልክተው፤ ግጭቱን ያባባሱ በርካታ ሰዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰዋል።
ከተፈናቀሉት ዜጎች መካከልም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን፤ የቀሩትንም ወደ ቀድሞ ቦታቸው በቅርቡ በመመለስ የማቋቋም ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ማጠቃለያ ላይ አዲስ አበባ ተቀምጠው በማያውቁትና በሌሉበት ቦታ በማኅበራዊ ሚዲያ እሳት የሚያራግቡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም በጥብቅ አሳስበዋል።