ኢትዮጵያ በመቋቋም፣ በመጠቀምና መግራት የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ አቅም ገንብታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመቋቋም፣ በመጠቀምና መግራት የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ አቅም ገንብታለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመቋቋም፣ በመጠቀምና መግራት የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ አቅም ገንብታለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲፕሎማሲው ዘርፍና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በመቋቋም፣ በመጠቀምና መግራት የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ አቅም ገንብታለች ብለዋል።
ዓለም በአሁኑ ወቅት በጣም ተለዋዋጭ፣ ኢ-ተገማችና በብዙ ዘርፎች ውስብስብ ባህሪ ይዟል ነው ያሉት።
በዚህ ውስብስብ፣ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነ አውድ ውስጥ በቋሚነት አንድ ወጥ መርህ ብቻ ማስቀመጥ እንደሚያስቸግር ጠቁመው፤ ዋናው መስፈሪያ ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለና ገቢር-ነክ (ተግባር ተኮር) የሆነ የዲፕሎማሲ አካሄድ መከተል እንደሆነ ገልጸዋል።
የእኛ መርህ የኢትዮጵያን የውሳኔ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ስኬት በኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ውሳኔዎች ውስጥ ሌሎች አካላት ተፅዕኖ እንዲያደርጉ አለመፍቀድ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በቀላሉ ሸብረክ የምትል ሀገር እንዳልሆነች በማንሳትም፤ በዓለም የዲፕሎማሲ ሒደት ውስጥ ሀገሪቱ የምትከተለው መርህ በሦስት 'መ'ዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል። እነርሱም
መቋቋም፦ ጠንካራ ተቋምና ሀገር መፍጠር፤
መጠቀም፦ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል መቀየር፤ እንዲሁም
መግራት፦ በሌሎች አካላት አጀንዳ ከመመራት ይልቅ የራስን አጀንዳ ቀርጾ መግራት መቻል ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእነዚህ በመቋቋም፣ በመጠቀምና በመግራት የዲፕሎማሲ መርሆች አማካኝነት ብሔራዊ ጥቅሟን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅ አቅም መገንባቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰፊው አብራርተዋል።