ቀጥታ፡

‎የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ተራ የድርድር ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኘ ታላቅ የሰላም ውጥን ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል

‎አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ተራ የድርድር ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኘ ታላቅ የሰላም ውጥን ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

በምላሻቸውም ‎የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ተራ የድርድር ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶችን ያስገኘ ታላቅ የሰላም ውጥን ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊ ወገኖች በእኩልነት ቁጭ ብለው የተወያዩበት መድረክ ነበር ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

መንግስት ወታደራዊ የበላይነት ከጨበጠ በኋላ የተሸነፈውን አካል በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጦ መደራደርና መፈራረም ብቻ ሳይሆን፣ በችግር ውስጥ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎችን ቀርቦ በመደገፍ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

በዚህ ስምምነት ምን ተገኘ ለሚሉ ወገኖች ቢያንስ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም መቻሉን እንደ ትልቅ ስኬት ማንሳት ይቻላል ብለዋል።

በተጨማሪም ከ60 ሺህ ያላነሱ ታጣቂዎች የዲዲአር (DDR) ክፍያ ተፈጽሞላቸው ከሰራዊቱ እንዲቀነሱ የተደረገ ሲሆን፣ በርካታ እስረኞችና ምርኮኞችም ተፈተዋል ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም