ከሕዝብ ጋር የተደረጉ ሰፊ የውይይት መድረኮች በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከሕዝብ ጋር የተደረጉ ሰፊ የውይይት መድረኮች በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ከሕዝብ ጋር የተደረጉ ሰፊ የውይይት መድረኮች በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከአገራዊ የውይይት መድረኮች በመካሄዳቸው በየአካባቢው ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶች በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ እውነታ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ሕዝቡና ብሔሮች "አንጋጭም" በማለት ግጭትን ሲቃወሙ፣ እነዚሁ ጸረ-ሰላም አካላት ራሳቸው እየመጡ ግጭት ለመፍጠር እንደሚሞክሩ አስታውቀዋል።
አሁን የሚስተዋሉ ችግሮች በአጋጭ ኃይሎች ሴራ የሚፈጠር መሆኑን ጠቁመው፤ በሕዝቦች መካከል ያለው ቅሬታ እምብዛም የማይታይና በእጅጉ የቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ መስተጋብር መፈጠሩም ትልቅ አገራዊ እርምጃ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የታሪክ ስብራት በርካታ እክሎችንና ጣጣዎችን ይዞ መምጣቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ያ እንዳይቀጥልና የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሕዝቡ ቅሬታውን በነጻነት አውጥቶ እንዲወያይበት መድረክ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም ይህንን የውይይትና የንግግር ሂደት ማጣጣል እንደማይገባና በርካታ አዎንታዊ ጉዳዮች የተገኙበት ለኢትዮጵያም በእጅጉ የሚጠቅም መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ተረጋግታና ጸንታ እንዳትኖር የሚፈልጉ የውጭና የውስጥ አካላት ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን አጥፍተው "ባንዳ" እንደሚያሳድዱ ገልጸው፤ ይህም ግጭት ለመፍጠር በጥቅመኛ ሴራ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ከ225 በላይ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን የጠቀሱ ሲሆን፣ ገዥው ብልፅግና ፓርቲም በየደረጃው ከአራት ሺህ በላይ የውይይት መድረኮችን መፍጠሩን ይፋ አድርገዋል።
በእነኚህ ከሕዝብ ጋር በተደረጉት ሰፊና አካታች የውይይት መድረኮች አማካኝነት በየጊዜው ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን በድጋሚ አረጋግጠዋል።