የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለዘላቂ ሰላም ሲባል የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለዘላቂ ሰላም ሲባል የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለዘላቂ ሰላም ሲባል የተከፈለ ትልቅ ዋጋ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጉዳይ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሰላም ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ግጭትን ለማቆም የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት መቋቋሙን ጠቁመው፤ የታጣቂዎች መልሶ ማቋቋም ከ60 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም የስልጠና በማሳለፍ እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ አሁንም የሰላም ማወክ ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ "እታገልልሃለሁ" በሚሉ ኃይሎች የተነሳ የትግራይ ህዝብ በሰላም ወጥቶ መግባት እንዳልቻለና የችግሩ ገፈት ቀማሽ እየሆነ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁከት ፈጣሪ አካላት ልጆቻቸውን ውጭ ሀገር እና አዲስ አበባ አስቀምጠው፣ በርካታ የትግራይ ወጣቶች በሱዳን ጦርነት እንዲሳተፉና ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባቸው እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በየጊዜው ጦርነት ለመቀስቀስ ጥረት ቢደረግም መንግስት በትዕግስት እያለፈው ይገኛል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።
መንግስት የሰላም መደፍረስ ምንጩን በሚገባ የሚያውቅ መሆኑን በመጠቆም፤ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት አስተማማኝ አቅም እንዳለውም አስረድተዋል።
የሀገሪቱ የጸጥታና ሕግ አስከባሪ ኃይሎች ከምንግዜውም በላይ በቁጥር፣ በጥራትና በቴክኖሎጂ አቅማቸውን በመገንባት በማንኛውም አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።