ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን የሚፈታና አዲስ የጋራ ማህበራዊ ውል የሚፈጸምበት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን የሚፈታና አዲስ የጋራ ማህበራዊ ውል የሚፈጸምበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን የሚፈታና አዲስ የጋራ ማህበራዊ ውል የሚፈጸምበት ነው ብለዋል።

አሁን የተገኘው የምክክር ዕድል ብዙዎች ዋጋ የከፈሉበት በመሆኑ ማቅለል እንደማይገባና ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ዕድል ሲመጣ አለመጠቀምና ካለፈ በኋላ የመጸጸት፣ እንዲሁም ሰው በሕይወት እያለ ዕውቅና ሳይሰጡ ሲሞት የማወደስ ክፉ አመል ሊቀየር እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ሀገራዊ ምክክሩ በችኮላ እየተካሄደ አለመሆኑንና በምክር ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶት በጥንቃቄ እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ምክክር ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ ከተደራጀ ተሳትፎና አጀንዳ የመነጨ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ጠቃሚ ሒደት ነው ብለዋል።

የምክክሩ ዋና ዓላማ ባለፉት ዘመናት የተከማቹትን ችግሮች በጋራ መክሮ መልክ ማስያዝ እንደሆነ በማስገንዘብ፥ አዲስ የማህበራዊ ውል የሚፈጸምበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በምክክሩ የሚፈቱት ችግሮች የቆዩ እንጂ አሁን የተፈጠሩ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግሮቹ አሁን ባለው መንግሥት ላይ የወደቁ የታሪክ አጋጣሚዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በመሆኑም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ፖለቲከኞች ከተዛባ አካሄድና አመለካከት ወጥተው ችግሮቹን በጋራ ለመፍታት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሕዝቡን ሐሳብ አቀናጅቶ ለመንግሥት እንደሚያቀርብ ጠቁመው፤ መንግሥትም ከቀረቡት ሐሳቦች ትምህርት በመውሰድና ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ጉዳዮች በጋራ በማፅደቅ ብሔራዊ መግባባትን እንደሚፈጥር አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም