7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታላቅነትና ለፈተናዎች የማይበገር መሆኑን ያሳየ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታላቅነትና ለፈተናዎች የማይበገር መሆኑን ያሳየ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30 /2018 (ኢዜአ)፦7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታላቅነትና ለፈተናዎች የማይበገር መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ምርጫውን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
በሰጡት ማብራሪያም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመማር ፈቃደኛ ለሆነ ለማንኛውም የፖለቲካ አካል ትልቅ ትምህርት የሰጠ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የረጅም ዘመናት ድልብ ሀብትና ጥበብ ያለው መሆኑን ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ሁሉ የሚለይበት አንድ ትልቅ ባህሪ እንዳለው በማስረዳት፤ "አትመዝገቡ፣ አትደግፉ እና አትምረጡ" የሚሉ እገዳዎችንና ማስፈራሪያዎችን ሳይበገር፣ ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት እስከ ሌሊት ድረስ የመረጠበትና ታላቅ ተጋድሎ የታየበት ምርጫ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው ምርጫ እንዳይሳካ የሚፈልጉ አካላት ምርጫውን ራሱን ኢላማ አድርገው መንቀሳቀሳቸውንም አውስተዋል። ባንዳዎችን የሚያሰማሩና የሚልኩ ኃይሎች ሁሉ ምርጫ ስለማይወዱ፣ ሂደቱ እንዳይካሄድ የቻሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም ነው ያሉት።
ችግርን መሻገርና ነገሮችን በብልሃት ማለፍ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ይህንን ሁሉ ፈተና ተሻግሮ በመምረጡና በማሸነፉ ትልቅ ክብር ይገባዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ "ጽንፈኝነትን፣ ባንዳነትንና ዘረኝነትን አንፈልግም፤ የጋራ ሀገርን ማልማትና ማበልፀግ ነው የምንፈልገው" የሚል መልዕክት በምርጫው በጋራ ማስተጋባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በምርጫው ወቅት ልጆቻቸው ጠንካራና ሰላማዊ ሀገር እንዲሁም ሀገረ መንግሥት ሊኖራቸው ይገባል የሚል የጸና አቋም የያዙ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም አረጋውያን፣ ሕሙማንና እናቶች፣ ጥይት እየተተኮሰባቸው እንኳ ሳይሸበሩ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፃቸውን መስጠታቸውን አስታውሰዋል። ይህ የዜጎች ቁርጠኝነት ለተመረጡ ሰዎችና ለመንግሥት ከፍተኛ አደራ የሰጠ መሆኑንም አክለዋል።
ሕዝቡ "ጅምራችሁን ወደንላችኋል፤ በውስጣችሁ ያሉ ሌቦችን አጥርታችሁ፣ አገልግሎትን አሻሽላችሁ፣ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችሁ ማስረከብ ትችላላችሁ" የሚል ዕድል ስለሰጠን፣ ሕዝባችንን በአግባቡ የማገልገል ትልቅ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የምርጫ ታሪክ፣ እንዲሁም “ምርጫ ከእኛ ወዲያ የለም” የሚሉ አካላት ጭምር አድርገውት በማያውቁት ልክ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ ጭቅጭቅና ክርክር አድርጎ ትልቅ ውሳኔ ማሳለፉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሠረት ፓርቲው በምርጫው 85 በመቶ በሆኑ ወንበሮች ላይ ብቻ በመወዳደር፣ ቀሪው 15 በመቶ ወንበር ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻቸውን እንዲወዳደሩበት ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል።
በምርጫው በርካታ ድምፆች እንዲሳተፉ ፍላጎት እንደነበርና በዚህም በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአጠቃላይ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሕዝብ ይሁንታ የታየበት ሆኖ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።