ቀጥታ፡

ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመድረስ የሚደረጉ ተጠባቂ ፍልሚያዎች፦ አርጀንቲና ከግብፅ፤ ስዊዘርላንድ ከኮሎምቢያ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30 /2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።

ምሽት አንድ ሰዓት ላይ አርጀንቲና ከግብጽ በአትላንታ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አርጀንቲና በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ኬፕቨርዴን 3 ለ 2 አሸንፋለች።

የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ከተጋጣሚዋ የበረታ ፉክክር ቢገጥማትም፣ ድል ቀንቷት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግራለች።

አርጀንቲና በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኳ ለ10ኛ ጊዜ ወደ 16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር አልፋለች።

ከዚህ በነበራት የዘጠኝ ጊዜ ተሳትፎ ሰባቱን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ስታልፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፋለች።

ተጋጣሚዋ ግብጽ ከአውስትራሊያ ጋር አንድ አቻ በመለያየት በመለያ ምት የ4 ለ 2 ድል በማስመዝገብ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 16 ውስጥ ገብታለች።

የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር በጥሎ ማለፍ ስታሸንፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አርጀንቲና እና ግብጽ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው ተገናኝተው አያውቁም።

እ.አ.አ በ2008 በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ አርጀንቲና 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ሰርጂዮ አጉዌሮ እና ኒኮላስ ቡርዲሶ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረው እና በ20 ጎሎች የውድድሩ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪ  ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታው የሚጠበቅ ተጫዋች ነው።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረውና በ20 ጎሎች የውድድሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሊዮኔል ሜሲ፣ በጨዋታው ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ተጫዋች ነው።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ኢማም አሹር እና አምበሉ መሐመድ ሳላህ በግብጽ በኩል የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

የጨዋታው አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከስዊዘርላንድ እና ኮሎምቢያ አሸናፊ ጋር ይገናኛል።

ስዊዘርላንድ ከኮሎምቢያ በቢሲ ፕሌስ ቫንኩቨር ስታዲየም ምሽት አምስት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ስዊዘርላንድ አልጄሪያን 2 ለ 0 አሸንፋለች።  ይህም ከ88 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበችው የጥሎ ማለፍ ድል ነው።

ተጋጣሚዋ ኮሎምቢያ ጋናን 1 ለ 0 በመርታት 16 ውስጥ ገብታለች። 

የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ በጥሎ ማለፉ ትጫወታለች።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።

አሜሪካ እ.አ.አ በ1994 ባዘጋጀችው 15ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ኮሎምቢያ 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ሄርናን ጋቪሪያ እና ሃሮልድ ሎዛኖ ግቦቹን በወቅቱ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።    

ሀገራቱ ከ32 ዓመታት በኋላ በጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተገናኝተዋል።

ቡድኖቹ በአጠቃላይ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ኮሎምቢያ በሁለቱ ድል ሲቀናት በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።




የስዊዘርላንድ እና ኮሎምቢያ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

ሞሮኮ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስፔን እና ቤልጂየም እስከ አሁን ሩብ ፍጻሜ የገቡ ሀገራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም