ቤልጂየም አሜሪካን በመርታት ሩብ ፍጻሜ ገብታለች - ኢዜአ አማርኛ
ቤልጂየም አሜሪካን በመርታት ሩብ ፍጻሜ ገብታለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ቤልጂየም አሜሪካን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።
ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሲያትል ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቻርልስ ደ ኬቴላሬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሃንስ ቫንከን እና ሮሜሎ ሉካኩ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ማሊክ ቲልማን የአሜሪካን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል።
አጥቂው ሮሜሎ ሉካኩ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሶስት አድርሷል። በአጠቃላይ ደግሞ በውድድሩ ላይ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ጎሎች ወደ ስምንት ከፍ አድርጓል።
ለቤልጂየም ብሔራዊ ቡድንም 93ኛ ግቡን አስቆጥሯል።
በጨዋታው ቤልጂየም ከፍተኛ ብልጫ ወስዳለች።
የተመለከተው ቀይ ካርድ በአነጋጋሪ ሁኔታ የተነሳለት የአሜሪካው አጥቂ ፍሎሪያን ባሎጉን በጨዋታው ላይ ተሰልፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ቤልጂየም ወደ ሩብ ፍጻሜ የገባች ሲሆን ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ከስፔን ጋር ትፋለማለች።
ከዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ የውድድሩ ጉዟዋ 16 ውስጥ ተገቷል።
አሜሪካ ከ24 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው ሩብ ፍጻሜ የመግባት ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።
ጣምራ አዘጋጅ የሆኑት አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በ16ቱ ዙር የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከውድድሩ ተሰናብተዋል።