ቀጥታ፡

ጥናቱ በየአካባቢው ያሉ የአምራች ኢንዱስትሪ እምቅ ጸጋዎችን በማወቅና በማልማት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)- የብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ የሀብት ልየታ ጥናት በየአካባቢው ያሉ የአምራች ኢንዱስትሪ እምቅ ጸጋዎችን በማወቅና በማልማት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ የሀብት ልየታ ጥናት ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አካሂዷል።

በመድረኩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ ለሀገራት ልዕልና መለኪያው የማምረቻው ዘርፍ የደረሰበት ደረጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማምረቻው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተውም ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ዕድገት ያለው ድርሻ ማደጉን፣ ገቢ ምርቶችን የመተካት ሂደት መሻሻሉንና የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ማደጉን ጠቅሰዋል።


 

የብሔራዊ አምራች ኢንዱስትሪ የሀብት ልየታ ጥናት በሀገር አቀፍ ደረጃ በየአካባቢው የሚገኙ እምቅ ሀብቶችን፣ መሠረተ ልማቶችንና ሌሎች ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን የተሟላ መረጃ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ የተሟላ መረጃ ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የአምራች ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት

ጥናቱ ወደፊት ለሚከናወኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚያመላክት ከመሆኑ በላይ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በስፋት ለመሳብ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የማምረቻ ዘርፉን ለማሳደግ፣ የኑሮ ውድነት ጫናን በዘላቂነት ለመቀነስና ፈጣንኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
 

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጥናቱ በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሀብቶችን ለማልማት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።


 

 
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በጥናቱ የተመለከቱ በየአካባቢው ያሉ እድሎችን ወደ ተጨባጭ ውጤቶች መቀየር የሚያስችሉ የጋራ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል።


ለትግበራው ስኬታማነት ሀገር አቀፍ መረጃዎችን ከሚያሰባስቡ ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የቅንጅት ስራዎች መጠናከር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።



የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጥናቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት የሆኑትን የግብርና እና የማዕድን ዘርፎች እምቅ አቅም ለመጠቀም የሀብት ልየታ መደረጉን አድንቀዋል።


በአስቻይ ሁኔታም የሰው ኃይልና መሠረተ ልማትን ታሳቢ ማድረጉ ጥሩ መሆኑን አንስተው፥ ሆኖም በየጊዜው ከሚቀያየሩ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።


 


የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የማምረቻው ዘርፍ በመደመር እይታ ከፍ ያለ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ፥ ጥናቱ የአምራች ዘርፍ ጸጋዎችን በማወቅና በመጠቀም ብልፅግናን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።


ጥናቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉንን ሀብቶች መረጃ በአንድ ማዕከል በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ማካተቱ ለማምረቻው ዘርፍ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።


ጥናቱን እንደ መነሻ በመውሰድ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ መረጃዎችን በማካተት በክልሉ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(/) በጥናቱ ሁሉን አቀፍ መረጃዎች መካተታቸው ለማምረቻው ዘርፍ ማደግ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ለባለሀብቶች በእውቀት ላይ የተመሠረተ የኢንቨስትመንት ውሳኔ ለመወሰንና ለቀጣይ የአምራች ዘርፍ ሥራዎች የተሻለ አቅም እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።


 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፥ በሁሉም አካባቢዎች ያሉትን ሀብቶች በማካተት ተደራሽነቱን በየጊዜው እያሳደገ እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ጥናቱ በሁሉም አካባቢዎች ያለውን ተጨባጭ መረጃ ለማወቅ፣ ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ፣ የምርት ግብዓትና ውጤትን ትስስር ለማጠናከር ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም