ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ ገጠር ቀበሌዎች የተጀመረው የሞዴል አርሶ አደሮች መንደር ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ጎንደር፤ ሰኔ 29/2018 (ኢዜአ)፡-በጎንደር ከተማ ገጠር ቀበሌዎች የተጀመረው ሞዴል የአርሶ አደሮች መንደር ግንባታ በአዲሱ በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡ 

ከተማ አስተዳደሩ በ2019 በጀት ዓመት አሻጋሪ የእድገትና የዘላቂ የልማት እቅድ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር የትውውቅ መድረክ ዛሬ አካሂዷል፡፡ 


 

በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ፕላንና ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ፋሲል አብዩ እንደተናገሩት የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ ሁለንተናዊ አገልግሎትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

የገጠር ኮሪደር ልማት መሰረተ ልማትን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እና የግብርናውን ኢኮኖሚ ለማዘመንም ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሳይ እና በሳቢያ የገጠር ቀበሌዎች በገጠር ኮሪደር የተገነባውን ሞዴል የአርሶ አደሮች መንደር በአዲሱ በጀት ዓመትም በሌሎች ቀበሌዎች ለማስፋት የቅድመ ዝግጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

 በአስተዳደሩ ስር በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች 20 ሞዴል የገጠር መንደሮችን ለመገንባት ዝግጅት መጀመሩንም አቶ ፋሲል ጠቅስዋል።

 የሚገነቡት ሞዴል መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይል፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ መንገድና ዘመናዊ ቤቶችን የሚያካትቱ ሲሆን፣ የግንባታ ቦታ መለየትን ጨምሮ ሀብት የማፈላለግ ሥራዎችን ለማከናወን እየተሰራ ይገኛል።

የሞዴል መንደሮቹ ግንባታ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፣ የአርሶ አደሮችንም የሥራ ባህል በመቀየር በኩል ጉልህ አስተዋጾ ያደርጋል ብለዋል።

ሞዴል መንደሮቹ አርሶ አደሩ መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኝ ያስችሉታል ያሉት ደግሞ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ነጻነት መንግስቴ ናቸው፡፡

መምሪያው በሞዴል መንደሮቹ ፣መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በቅርበት ለመፍታት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ እና የክፍለ ከተማ የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም