ህገወጡ የህወሓት ቡድን ሕጻናትና ሲቪሎችን በአፈሳና በግዳጅ ለጦርነት እየመለመለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህገወጡ የህወሓት ቡድን ሕጻናትና ሲቪሎችን በአፈሳና በግዳጅ ለጦርነት እየመለመለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ ከህገወጥ የወርቅ ሽያጭ ሰዎችን አግቶ ወደ መሸጥ አረመኔያዊ ተግባር የገባው ህገወጡ ህወሓት በትግራይ ክልል ሲቪሎች እና ሕጻናትን እያፈሰና እያስገደደ ለጦርነት እያዘጋጀ መሆኑን ሒውማን ራይት ዋች አጋለጠ።
ሒውማን ራይት ዋች ዛሬ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ሲቪሎችን ጨምሮ እድሜያቸው ገና 15 ዓመት ያልደረሱ ህጻናትን ህገወጡ የህወሃት ቡድን በግዳጅ ለውትድርና እየመለመለ ይገኛል።
በመንገድ ላይ፣ በቢሮዎች ውስጥ፣ በሌሊት ከቤት ወደ ቤት በሚደረጉ ህገወጥ ፍተሻዎች እንዲሁም ለክልሉ ወጣቶች ዋነኛ የሥራ ዕድል ምንጭ ከሆኑት የወርቅ ማዕድን ማውጫ ቦታዎች ጭምር ህፃናትን እያገተ እንደሚገኝም ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ ሒውማን ራይትስ ዋች ገልጿል።
ቡድኑ ሲቪሎችንና ሕጻናትን በሃይል ወደ ጦርነት ለማስገባት የሚያካሂደው ዘመቻ በክልሉ የፍርሃት ድባብ እንዲፈጠር አድርጓል ብሏል ሒውማን ራይትስ ዋች በድርጅቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ሌቲሺያ ባደር በኩል።
ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ይህንን የግዳጅ ምልመላና በዚህ ዘመን የማይጠበቅ አረመኔያዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተግባር አጠናክሮ መቀጠሉን የዓይን እማኞች እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የቤተሰብ አባላት ያረጋገጡ ሲሆን፣ አፈናው መጠነ ሰፊና አስገዳጅ መሆኑንም መስክረዋል።
የአፈናና እገታ ዘመቻው በጎዳናዎች፣ በገበያዎች እና በወርቅ ማዕድን ማውጫ ቦታዎች በተደረጉ የጅምላ አፈሳዎች ተጠናክሮ መቀጠሉም በሪፖርቱ ተገልጿል።
ሒውማን ራይት ዋች ዋቢ ባደረገው መረጃ ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች እንደተናገሩት፣ የህገወጡ ቡድን ባለሥልጣናት የቀድሞ ተዋጊዎችን ዝርዝር በመያዝ የሰፈር መረጃ አቅራቢዎችን (የሰፈር ሰላዮችን) ተጠቅመዋል ብሏል።
ከዚህም አልፎ ወጣቶች ከምልመላው ለማምለጥ አካባቢያቸውን ለቀው ሲሰደዱ፣ የቡድኑ ሀላፊዎች የታዳጊዎቹን ቤተሰቦች (እናቶችን ጨምሮ) በማሰር እና በማንገላታት ቤተሰብ ላይ የጅምላ ቅጣት እየፈጸሙ መሆኑን ሪፖርቱ በስፋት አብራርቷል።
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ፤ ይህ የግዳጅ ምልመላ ድርጊት የ1949ኙን የጄኔቫ ስምምነት የሚጥስ እና በተለይም ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በጦርነት ውስጥ ማሳተፍ የጦር ወንጀል መሆኑን አሳስቧል።
የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚደግፉ እንደ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት፤ የቡድኑን የግዳጅ ምልመላ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና የታፈኑ ሕጻናትንም እንዲለቁ ጠንካራ ጫና ሊያደርጉ እንደሚገባ ሂውማን ራይትስ ዎች አሳስቧል።