ቀጥታ፡

በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና የጎላ ነው- ከንቲባ ጥራቱ በየነ

‎ሀዋሳ ሰኔ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በሀዋሳ ከተማ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና የጎላ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለፁ።

‎የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2017/18 ግብር ዘመን ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የዕውቅናና ሽልማት እንዲሁም የ2018/19 ግብር ዘመን የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በከተማዋ ከግብር ከፋዮች በሚሰበሰብ ገቢ የነዋሪዎችን ፍላጎት የሚያሟሉ ለትውልድ የሚሻገሩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ታማኝ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ በመክፈል በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ከንቲባ ጥራቱ አክለውም የከተማዋ ግብር ከፋዮች ከመደበኛ የግብር ግዴታቸው ባሻገር በከተማዋ ለሚከናወነው የኮሪደርና ሐይቅ ዳርቻ ልማት ድጋፍ በማድረግም አሻራቸውን እያኖሩ እንደሚገኙ አውስተዋል።‎

በከተማዋ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓም ጀምሮ በሚከናወነው የቀጣዩ ግብር ዘመን ገቢ አሰባሰብ ላይም ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልኩ ማርቆስ በበኩላቸው በከተማዋ ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አኳያ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት በየዓመቱ እያደገ የሚሄድ መሻሻል እየተመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።‎

በ2017/18 ግብር ዘመን 6 ነጥብ 4 ቢሊዮብ ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከእቅድ በላይ 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አመልክተዋል ።

ለዚህ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በወቅቱና በአግባቡ የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች የጎላ ድርሻ መወጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የስነ ስርአቱ ዓላማ ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችን ለማበረታታትና ሌሎችም የነርሱን አርአያ እንዲከተሉ መነሳሳት ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ዕውቅናና ሽልማት ከተበረከተላቸው ግብር ከፋዮች መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ተስፋዬ ፀጋዬ በተሰጣቸው ዕውቅናና ሽልማት መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት በላቀ ደረጃ በታማኝነትና በወቅቱ ግብራቸውን በመክፈል በከተማዋ በሚከናወነው የልማት ሥራ ላይ የላቀ አስተዋፅዖ ለማድረግ ያነሳሳቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ አብርሃም ኮላቶ በበኩላቸው ከግብር ከፋዮች በሚሰበሰብ ገቢ ለትውልድ የሚሸጋገሩ መሰረተ ልማቶች የሚገነቡ በመሆኑ በግብር ከፋይነታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በስነ ስርአቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩና የክፍለ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች፣ ግብር ከፋዮችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም