ቀጥታ፡

28ኛው የዓለም አቀፍ የሐረሪ ባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል በአሜሪካዋ ሜምፊስ ከተማ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፡- በርካታ የሐረሪ ማኅበረሰብ አባላት መዳረሻ በሆነችው በአሜሪካዋ ሜምፊስ ከተማ፤ 28ኛው ዓለም አቀፍ የሐረሪዎች የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል በተለያዩ ማራኪ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው።

ዓለም አቀፉ የሐረሪዎችን ቀን መከበሩ ባህላችንን ፤ታሪካችንን፤ ቋንቋችንን እና ቅርሶቻችንን በሚገባ በማወቅ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።


 

በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅና ዳያስፖራዎችም ከአገራቸው ጋር ያላቸው ትስስርና ተሳትፎ ይበልጥ የሚጎለብቱበት እንዲሁም በኢንቨስትመንትና በማህበራዊ ዘርፎች በንቃት እንዲሳተፉ አድርጓል።

በተለይ የፌስቲቫሉ መከበር በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የሐረሪ ብሄረሰብና ወዳጆች አንድ ላይ በመሰባሰብ ይበልጥ ትስስራቸውን የሚጠናክሩበት እና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የአገሪቱን ጥሩ ገጽታ እንደሚገነባ ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ ተወላጆች እና ወዳጆች ባላቸው እዉቀትና ልምድ የአገራቸውን መልካም ገፅታ እንዲገነቡ ከማስቻሉም ባሻገር በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የሚያደርጉትን ድጋፍና ተሳትፎ በማሳደግ ረገድም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።


 

በአሜሪካ ሜምፊስ ከተማ እየተካሄደ የሚገኝው 28ኛው ዓለም ዓቀፍ የሐረሪ የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል በቀጣይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ከወጣው መርሐ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

የሐረሪ ባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ከቀናት በፊት በአሜሪካ ሜምፊስ ከተማ የከተማዋ በዓል ሆኖ እንዲከበር የከተማው ምክር ቤት በአዋጅ መደንገጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም