ቀጥታ፡

በክልሉ በመኸር እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ቦንጋ፤ ሰኔ29/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመኸር እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

በክልሉ በመኸር እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የማሳ፣ የግብዓትና መሰል ዝግጅቶች መደረጋቸውም ተመላክቷል።

የክልሉን ያለፈው ዓመት የመኸር አርሻ አፈጻጸም ለመገምገምና የዘንድሮውን የመኸር ግብርና በማስመልከት የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በመድረኩ እንደገለጹት፣ በክልሉ የመኸር እርሻን ስኬታማ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች በተቀናጀ መልኩ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በየደረጃው ለአርሶ አደሩ የሚደረገውን ድጋፍና ክትትል በማጠናከርና የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለመኸር እርሻው ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ መቅረቡን አቶ ማስረሻ ጠቁመው፣ በልማቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍና ክትትሉ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ በክልሉ በመኸር ወቅት ከ463ሺህ ሄክታር ማሳ በአዝርት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚሸፈን ሲሆን ከልማቱም ከ20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የግብርና መምሪያ ሃላፊዎችም በመኸር እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብርና ቴክኖሎጂ ፣ለማሳ ዝግጅትና ለግብአት አቅርቦትና አጠቃቀም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።  


 

ከሀላፊዎቹ መካከል የዳውሮ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ሥራ መምሪያ ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር በተላ በየነ እንደገለጹት፣ የመኸር እርሻን ስኬታማ ለማድረግ የአርሶ አደሩን የግብርና ግብአት አጠቃቀም ከማሻሻል በተጨማሪ የድጋፍና ክትትል ሥራው ይጠናከራል።

በዞኑ ከ90ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸሩ ለማልማት መታቀዱን ገልጸው፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል።

ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ሜካናይዜሽን እና ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ሥራ መምሪያ ሀላፊ አቶ ገረመው ገብሬ ናቸው።


 

በዞኑ 139 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው፣ የታቀደውን ለማሳካት ግብአት ከማቅረብ ባለፈ የባለሙያዎች ድጋፍና እገዛ ይጠናከራል ብለዋል።


 

የሸካ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ሥራ መምሪያ ሀላፊ አቶ አይምሮ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በዞኑ ዘንድሮ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የማሳ፣ የግብዓትና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም