በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር ጠንካራ መሰረት እየጣለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር ጠንካራ መሰረት እየጣለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር ጠንካራ መሰረት መጣል መቻሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
በምክር ቤቱ የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ 2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል።
የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ ኃይሉ ኢፋ ባቀረቡት ሪፖርት የፊስካል ሽግግሮችን በፍትሐዊነት እና በውጤታማነት ለማስፈጸም የሚያግዙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የአቅም ግንባታ፣ የጋራ ገቢዎች ክትትል፣ የጥቅል ድጎማ ቀመር ማሻሻያ ዝግጅት እና የውስን ዓላማ ድጎማዎች ላይ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በጠንካራ ክትትል፣ በየጊዜው የአፈጻጸም ግምገማ በማድረግ እና በመደገፍ ወደ ከፍተኛ ተቋማዊ ውጤት ማሸጋገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ክልሎችን ለመደገፍ ያከናወኑት ሥራ አመርቂ ውጤት እና ጠንካራ የሀብት አስተዳደር የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለውጡ ፍትሐዊ ግልጽነት የታከለበት ስርዓት እንዲኖር ማስቻሉን ገልፀው፤ ሀብቶች ስራ ላይ መዋላቸውን መከታተል እንደሚገባ አመላክተዋል።
የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሽመልስ አብዲሳ በግልጽነት፣ ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ ፍትሐዊ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን በማስፋፋት በኩል ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን እና አዳዲስ አሠራሮች መዘርጋታቸውን ገልጸው፥ የነበሩ ክፍተቶችም መቀረፋቸውን ጠቁመዋል።
ክልሎች ከድጎማ ጎን ለጎን የራሳቸውን የልማት አቅም ለማሳደግ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አንስተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር ጠንካራ መሰረት መጣል መቻሉን ጠቁመዋል።
ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭትን በማስፋፋት በኩል የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።