ቀጥታ፡

የሀገሪቱን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለማፋጠን አካባቢዎችን ወደ ዲጂታል አድራሻ ሥርዓት የማስገባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ የሀገሪቱን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለማፋጠን የተለያዩ አካባቢዎችን ወደ ዲጂታል አድራሻ ሥርዓት የማስገባት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ምጣኔ ሀብታዊ እና ልማታዊ ዕድገት እንዲሁም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025/2030” ስትራቴጂን ቀጣይነት ባለው መንገድ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላቸው ፀሐይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሀገሪቱ ወደ ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም ወደ ስማርት ሲቲነት ለመቀየር በከፍተኛ ግስጋሴ ላይ የምትገኝ መሆኗን ገልጸዋል።

መንግሥት ለዲጂታላይዜሽን ጉዞ መሠረት የሆኑ ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፣ ዜጎች ከቴክኖሎጂው ጋር አብረው መራመድ የሚችሉበትን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ለአብነትም የኢትዮ-ኮደርስ አምስት ሚሊዮን ዜጎች ስልጠና ሰፊ መድረክ መመቻቸቱን ጠቅሰው ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች የሚደገፉበት ምቹ መደላድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

የተለያዩ ተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማስፋት የመንግሥት አገልግሎቶችን፣ የንግድ ሥርዓቶችን እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ እንዲያዘምኑ መንገድ መከፈቱንም ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት መዘርጋት ሀገሪቱ ወደ ስማርት ከተማነት ለምታደርገው ግስጋሴ ስኬት ወሳኝ በመሆኑ፤ ኢንስቲትዩቱ በትኩረት ሲሠራበት መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ወደ 40 የሚጠጉ አከባቢዎች ወደ ዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ ዘጠኝ ከተሞችን ወደ ዲጂታል አድራሻ ለማስገባት የሚያስችሉ መረጃዎች መሰብሰባቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ በተለያዩ ከተሞች የተገነቡ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓቶች ቀድመው ወደ አገልግሎት ገብተዋል።

የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት መዘርጋቱ ዜጎች በቴክኖሎጂ የተደገፉና ዘመኑን የዋጁ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

በመሆኑም የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን፣ የተለያዩ አካባቢዎችን ወደዚህ ዘመናዊ አድራሻ ሥርዓት የማስገባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም