ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባኤ የሚመከርባቸው ዐበይት አጀንዳዎች የወጣቶችን የተሻለች ሀገር ግንባታ መሻት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባኤ የሚመከርባቸው ዐበይት አጀንዳዎች የወጣቶችን የተሻለች ሀገር ግንባታ መሻት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የወጣት አደረጃጀት ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በስልጡን የምክክር መፍትሔ ለመስጠት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተሰናድተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ከሚቀጥለው ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤም ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና መልካም አስተዳደርና ሰላም ግንባታም የምክክር ሂደቱ ዐበይት አጀንዳዎች ናቸው።

የዮቡንቱ  ወጣቶች ለሰላም ጥምረት ሰብሳቢና  የጣምራ ማህበራዊ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ይርጋለም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክር በዜጎች መካከል ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በተጀመረ ማግስትም የወጣቶችን ተሳትፎና ግንዛቤ በማሳደግ በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ገንቢ ሚና መወጣታቸውን ገልጿል።

የምክክር ሂደቱ አሳታፊና አካታችነትም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትና ዕድገትን ለማሳለጥ የሚያስችል የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን ተናግሯል።

ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያስረከቧቸው አጀንዳዎችም በዋናው ጉባኤ በሚመከርባቸው ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ሥር በንዑስ አጀንዳነት መካተታቸውን አንስቷል።

ይህም ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን በመገንባት ወጣቶች በሀገራቸው የዘላቂ ሰላም ግንባታና ልማት የሚኖራቸውን ገንቢ ሚና የሚያሳይ መሆኑን አስረድቷል።

በዋናው ጉባኤ የሚመከርባቸው ዐበይት አጀንዳዎችም ዘላቂ ሰላምና መግባባትን ለመፍጠር እንደሚረዱ በመጥቀስ፤ የዋናው ጉባኤ የህዝብ ተወካዮችም በኃላፊነት መንፈስ መመካከር እንዳለባቸው አስገንዝቧል።  


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርቢርሳ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ምዕራፍ የወጣቶች ተሳትፎ የተረጋገጠበት ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም የዘመናት የተዛቡ ትርክቶችንና የሀገራዊ መግባባት መዛነፎችን  በማረቅ የወጣቶችን ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን የሚያሳልጥ መግባባት ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል።

የእስካሁኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደት አካታችና አሳታፊነትም ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የመፍትሔ አካል መሆናቸውን  በተግባር እንዳስመሰከረ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባኤ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችም የተናጠል ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሳይሆኑ በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስቷል።

በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተለዩ ዐበይት አጀንዳዎችም የሀገርን ችግር ክብደትና ቅለት ታሳቢ በማድረግ የተቀረጹና የወጣቶች የተሻለ ሀገር ግንባታ መሻት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን አስገንዝቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም