ቀጥታ፡

በአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን ጠንካራ የዕፅዋት ጤና ጥበቃ ሥርዓት መገንባት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ አህጉር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ውጤታማ የዕፅዋት ጤና ጥበቃ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

"የእፅዋት ሀብቶችን እና ተቋማትን ለመጠበቅ የአፍሪካ ሀገራትን በሳይንስ እና በዲጂታል መሳሪያዎች ማብቃት" በሚል መሪ ኃሳብ የተዘጋጀው የአፍሪካ ዕፅዋት ጤና ጥበቃ ፕሮግራም የስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አፍሪካ ግብርናውን ለመለወጥና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የምታደርገው ጥረት በድንበር ተሻጋሪ ተባዮች፣ በወራሪ ዝርያዎች፣ በድንገተኛ በሽታዎች እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል።

እነዚህ ተግዳሮቶች በምርት፣ በብዝሃ ሕይወት እና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው፣ በእፅዋት ጤና ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ስኬት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። 

ተባይና የእፅዋት በሽታዎች በድንበር የማይገደቡ በመሆናቸው፣ የትኛዋም ሀገር ተግዳሮቶቹን ብቻዋን መፍታት ስለማይቻል አህጉራዊ የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጠንካራ የዕፅዋት ጤና ጥበቃ ሥርዓት መገንባት የግብርና ኢንቨስትመንቶችን ለመጠበቅ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርን ለመንከባከብ መሠረታዊ መሆኑን አስገንዝበዋል። 

በተጨማሪም ደህንነቱ የተጠበቀና ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትን ለማመቻቸት እንዲሁም የምግብ ሥርዓትን የመቋቋም አቅም ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያም ዘላቂ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የዕፅዋትን ጤና የመጠበቅ ተግባር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።


 

የዓለም አቀፉ የዕፅዋት ጥበቃ ኮንቬንሽን ጸሃፊ ኤንሪኮ ፔሮቲ በበኩላቸው ድርጅቱ ጠንካራ እና የበለጠ የመቋቋም አቅም ያለው የዕፅዋት ጤናን ለመገንባትና የምግብ ዋስትናን ለመደገፍ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

አጋርነቶችን ማጠናከርና አዳዲሶችን መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው፣ በአፍሪካ የዕፅዋት ጤና ፕሮግራም በኩል የተመዘገበው አስደናቂ እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ የላቀ ተፅዕኖ ለመፍጠር መሠረት መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኢንተር-አፍሪካን የዕፅዋት ጤና ጥበቃ ምክር ቤት አስተባባሪ ሳሊው ኒያሲ (ዶ/ር)፤ ተቋማቸው ለብሔራዊ ተቋማት የክትትል፣ የላቦራቶሪ ምርመራና የመከላከል አቅምን በማሳደግ፤ በሳይንስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥንና ቀጣናዊ የመረጃ ልውውጥን እያጠናከረ ይገኛል ብለዋል።


 

ይህ ፕሮግራም የአፍሪካ ህብረትን የዕፅዋት ጤና ስትራቴጂ ትግበራ የሚደግፍ እና በአካታች የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም ስር የተገለጹትን የአጀንዳ እ.አ.አ 2063 ለማሳካት እየተሰሩ ካሉት ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።   

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ጊዜያዊ ተወካይ ኦርላንዶ ሶሳ በበኩላቸው፣ ለስኬቱ የመንግስታት፣ የቀጣናዊ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የቴክኒክ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ የተቀናጀ አጋርነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የገንዘብ ድጋፍ፣ የቴክኒክ እውቀት፣ ስልጠና፣ የምርመራ አገልግሎት፣ የዲጂታል ድጋፍ ጋር የተያያዙ አስተዋፅኦዎች ተቀናጅተው ዘላቂ አቅምን ለመገንባት መዋል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮች እና በዕሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ላሉ ተዋናዮች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም