የሴቶችና ህጻናትን ደህንነትና ጤና ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው- ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር)/ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ህጻናትን ደህንነትና ጤና ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው- ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር)/
ባህርዳር፣ሰኔ 29 /2018(ኢዜአ)፡- በችግር ውስጥ የሚገኙ ሴቶችንና ህጻናትን ወደ ማእከል በማስገባት ወደ ቀድሞ ሒወታቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር )ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ የተገነባው የሴቶችና ህጻናት ማገገሚያ ማዕከልን ወደ ስራ የማስገባት መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።
የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ተጎጂዎችን በመቀበል የጤና፣ የስነ-ልቦና ህክምናና ሌሎች እንክብካቤዎችን በማድረግ ወደ ቀድሞ ሒወታቸው እንዲመለሱ የሚሰራ ነው።
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች በችግር ወስጥ የሚገኙ ሴቶችንና ህጻናትን ወደ ማዕከሉ በማስገባት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የሀይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ተቋማትና መላው ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ነው ያሳሰቡት።
የማገገሚያ ማዕከሉ በ123 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ናቸው።
በዚህም ከባህር ዳር ከተማ በተጨማሪ ከደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅ ፣ ሰሜንና ምእራብ ጎጃም ዞኖችና አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ለሚመጡ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።
ማዕከሉ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን አክሞ እንዲያገግሙ ከማድረግ ባሻገር የሙያ ስልጠና ወስደው የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ማእከሉ ለአንድ ዓመት ሕክምና በማድረግ እንዲቋቋሙ የሚሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ማዕከሉ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ምቹና ሰላማዊ የስራ አካባቢ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ።
አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይም ውይይት ተካሂዷል።