ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ ተገለጸ፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 17 እና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 81 ንዑስ አንቀፅ 1 እና 3 መሠረት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለስልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈፃሚውን አካል አሠራር የመመርመር፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን አለው፡፡

በዚሁ ሕገ መንግሥትና የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ መሠረት 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በሚያካሂደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ተገኝተው የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ በጀት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘም ምክር ቤቱ ፣ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ የበጀት አዋጁን እንደሚያፀደቅ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም