ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጎተራ ማሳለጫ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።


 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሁሉም መስክ ተጨባጭ ሀገራዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ መሰረት እየጣለ ነው።

የተሸረሸሩ እና የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ አስችሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በምግብ ራስን የመቻል ግቦችን በማሳካት ረገድ አዎንታዊ ውጤቶች እየተመዘገበበት ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ በንቃት መሳተፉን ጠቅሰው፤ በ2018 በጀት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ እና በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያጎሉ ተግባራትን በሰፊው እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የወሰደችው የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራዊ ምላሽ ስሟን በዓለም መድረክ ከፍ ማድረጉን አስረድተዋል።


 

ከዚህም ባለፈ ስለ አፍሪካ የሚነሱ የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል ከፍያለ አህጉራዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ የደን ሽፋን እንዲጭምር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሁሉም በየአካቢው ችግኞችን በመትከል ሀገራዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የፕላንኒንግ ዳይሬክተር መሳይ አበበ እንደገለጹት፤ ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ለቀጣዩ ትውልድ ዋስትና ነው ያሉ ሲሆን፤ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ለውጤት ማብቃት ከኛ ይጠበቃል ብለዋል።


 

አሻራዬን በማኖሬ እኮራለሁ ያሉት የአገልግሎቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ማስተዋል ገዳ፤ የምንተክለው ችግኝ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋን ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

በቀጣይም የአረንጓዴ ዐሻራ ዘላቂ ግቦች እንዲሳኩ የሚጠበቅብኝን እወጣለሁ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም