ቀጥታ፡

በክልሉ የሕጻናትን መብትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ሥራን ማጠናከር ይገባል

አዳማ፣ ሰኔ 29/2018 (ኢዜአ):-በክልሉ የሕጻናት መብትና ደህንነትን በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማጠናከር ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ተገለጸ። 

የአፍሪካ ሕፃናት ቀን በክልል ደረጃ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገዛሊ አባሲመልን ጨምሮ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና አመራሮች በተገኙበት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተከብሯል።


 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገዛሊ አበሲመል እንዳሉት፤ ዛሬ በሕጻናት ላይ የሚሰራው ኢንቨስትመንት ነገ ሰላሟ የተረጋጋና የለማች ሀገር እውን ለማድረግ መሰረት ነው። 

በመሆኑም በክልሉ የሕፃናትን መብትነና ደህንነት በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ይሄን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት የጀመሩትን ሥራ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል። 


 

በተለይ ለሕጻናት የሚሰጠው ነፃ የህግ አገልግሎትና ጥበቃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፍትህ ተቋማት በቅንጅት የሚያከናውኑትን ተግባር ማስቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሕጻናት ለአደጋ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የዕለት ተዕለት እገዛና ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልሉ መንግሥት የተጀመሩ የሕፃናት መዝናኛ ማዕከላት፣ መዋያ እና ማቆያዎች ልማት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት አቶ ገዛሊ፣ ሕጻናት ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ አግኝተው በስነ ምግባር እንዲያድጉ በጋራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

በጨፌ ኦሮሚያ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መስታወት ፈይሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የሕፃናት ደህንነትና መብትን ለማስጠበቅ፣ ወደትምህርት ቤት ለማምጣትና ፍላጎታቸውን ለማሟላት በትብብር መስራት ይገባል። 

ሕጻናትን በስነ-ልቦና ለመገንባትና በስነ-ምግባር ለማነፅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲረባረቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ በበኩላቸው እንዳሉት የሕፃናት ደህንነትና መብትን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። 


 

የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በስነ-ምግባር ለማነፅ ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ህጻናት ወደትምህርት ቤት እንዲመጡ ከማድረግ ባለፈ እነሱን የሚጎዱ ጎጂ ልማዳዊ ደርጊቶችን ለማስወገድ በትብብር ይሰራል ሲሉም አስታውቀዋል። 

በብልጽግና ፓርቲ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አጀማ እንደገለጹት፤ ተተኪው ትውልድ በትምህርትና በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተጨባጭ ሥራዎች ተሰርተዋል።


 

ለእዚህም በከተማዋ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት የተሰራውን ሥራ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ ሕጻናት ፓርላማ ፕሬዚዳንት ተማሪ ሐያት ሙሐመድ በበኩሏ፤ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እንዲቆምና ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት መማር እንዲችሉ በክልሉ መንግሥት እየተሰራ ባለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግራለች።


 

ይሁን እንጂ የሕጻናት ጉዳትና ተጋላጭነትን ለመቀነስ አሁንም በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጻ፣ በየደረጃው የሚገኙ የሕፃናት ፓርላማዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ብላለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም