ቀጥታ፡

በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ክህሎት በማሳደግ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አግዟል

ሆሳዕና፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ክህሎት በማሳደግ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ማገዙን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ሀላፊ ሰላሙ አማዶ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ክህሎትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻለ ነው።

ወጣቶቹም በስልጠናው ራሳቸውን በማብቃት ከሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ካሉ ካምፓኒዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

በስልጠናው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ ወጣቶችን ከገበያው ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ ከተቀላቀሉ ወጣቶች መካከል ጫኪሶ ወልዴ አንዱ ሲሆን በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ያገኘው እውቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ተናግሯል።

ይህም ከሥራ ጠባቂነት ይልቅ የራሱን ስራ በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እንሚያጠናክርለት ገልጿል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት የወጣቶችን ሥራ ፈጣሪነትና ተወዳዳሪነት በማረጋገጡ ሌሎችም የእሱን ተሞክሮ እንዲወስዱ መክሯል።

ሌላኛው ወጣት አብይ ላቀው በበኩሉ በኢትዮ ኮደርስ መርሃ ግብር የወሰደው ስልጠና በዘርፉ የነበረውን እውቀት ይበልጥ ለማሳደግ እንዳስቻለው ተናግሯል።

ስልጠናው በኦን ላይን ገቢ በማመንጨት ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለውን በቂ እውቀት ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለትም ጠቁሟል።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ ሥራዎችን በቤቱ ሆኖ በኦን ላይን በመስራት ገቢ ማግኘት መጀመሩን ነው የገለጸው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ከ242ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ተከታትለው የእውቅና የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም