በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የፖለቲካ ተሳትፎና የምርጫ ሂደት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት የሚያስችል ጥሩ መሰረት እያኖረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የፖለቲካ ተሳትፎና የምርጫ ሂደት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት የሚያስችል ጥሩ መሰረት እያኖረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየጎለበተ የመጣው የፖለቲካ ተሳትፎና የምርጫ ሂደት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት የሚያስችል ጥሩ መሰረት እያኖረ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብላጫ የምክር ቤት ድምፅ ላገኘው ብልጽግና ፓርቲ የመልካም ምኞት መልዕክቶች ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች ባስተላለፉት መልዕክት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ አሳታፊ እና አካታች በሆነ መልኩ ጠንካራ ፉክክርና የላቀ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን አንስተዋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲዎች በሃሳብ የበላይነት የተፎካከሩበትና በሰለጠነ አግባብ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጥሩ መሰረት እያስቀመጠ መሆኑን አመራሮቹ ይናገራሉ።
ከምርጫ ፉክክሩ ማግስት ጀምሮ የህዝብን ውሳኔ የመቀበል ዝግጁነትን ከማሳየት ባለፈ በትብብር ሀገረ መንግስት የመገንባትና ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም መከበር ጠንካራ አቋም ይዞ የመስራት ልምድ እየዳበረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከል የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ ታሪኩ ድንበሩ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎና የምርጫ ሂደት መሰረታዊ ለውጥ የመጣበት መሆኑን ተናግረዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበረው አጠቃላይ የምርጫ ሂደትም ይህንኑ በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸው ፉክክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የምርጫ ቦርድን ውጤት በመቀበል በቀጣይ በትብብር ሀገር ለመገንባት በጋራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ኤርሚያስ ተገኔ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሟላ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምርጫ በኋላም ሀገር የምትቀጥል በመሆኑ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማራመድ እንዳለባቸው አንስተው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቀጣይነት እንዲኖረው ፓርቲያችን የበኩሉን ኃላፊነት መወጣቱን ይቀጥላል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ ኢደኤ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰለጠነ አግባብ መሰረታዊ የፖለቲካ ባህል ለውጥ ያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ድምፅና በሀሳብ ልዕልና ብቻ ሥልጣን መያዝ እንደሚቻል በማመን ከፉክክር ማግስት ውጤቱን በመቀበል በትብብር ሀገር ግንባታ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።