ቀጥታ፡

ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ማካሄድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ ዋናውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ማካሄድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ከሐምሌ ስምንት ጀምሮ የሚካሄደውን ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል በሚካሄደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤ ከወረዳ፣ ክልል፣ ፌዴራልና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በድምሩ 4 ሺህ ተወካዮች እንደሚታደሙ አስታውቀዋል።

ለዋናው ጉባኤ ተሳታፊዎችም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ምቹና አስተማማኝ የሕፃናት ማቆያ፣ ትራንስፖርት፣ ጤና፣ ምግብ፣ የማረፊያና ልዩ ልዩ የአገልግሎት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የመሰብሰቢያና የመመካከሪያ ስፍራዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአቅመ ደካሞችና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተሳታፊዎች ምቹ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ልዩ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።

የዋናው ጉባኤ ተሳታፊዎችም በምክክር ጊዜ ቆይታቸው ምንም ዓይነት የመስተንግዶ ክፍተት እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓትም በልዩ መርሃ ግብርና ሀገራዊ አንደምታውን በሚመጥን መልኩ ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የምክክር ሂደቱ ሥነ-ዘዴ መሠረትም ተሳታፊዎች በተለያዩ የምክክር ቡድኖች ሆነው በአጀንዳዎች ላይ ጥልቀት ያለው ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚረዱ የመመካከሪያ ሥፍራ ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።

በአጠቃላይም ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር በተወካዮቻቸው አማካኝነት እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚመክሩበት ታላቅ መድረክን ስኬታማ የሚያደርጉ ተግባራት መሠራታቸውን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የጉባኤው ተሳታፊዎች እየተላለፈ ባለው ጥሪ መሠረት እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት ለኮሚሽኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም