የዩኒቨርሲቲ፣ የሆስፒታሎችና የኢንዱስትሪ ትስስር ለአፍሪካ ጤና ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲ፣ የሆስፒታሎችና የኢንዱስትሪ ትስስር ለአፍሪካ ጤና ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፡- ለአፍሪካ የጤና ዘርፍ ዕድገት የዩኒቨርሲቲዎች፣ የሆስፒታሎችና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት «MedEDAfrica 2026» አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ በይፋ ከፍተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ በሕክምና ትምህርትና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉሪቱን የነገ ተስፋ ለመቅረጽ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን ገልጸው፣ የአፍሪካ የነገ ጤና እና ተስፋ ዛሬ በሚዘጋጀው ወጣት የሕክምና ኃይል ላይ እንደሚወሰን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና ባለሞያዎችን ትምህርት ለማስፋፋት ከፍተኛ ሙዓለ ንዋይ ማፍሰሷንና ያልተማከለ ሥርዓት መዘርጋቷንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ከአፍሪካ ሀገራት የመጡ የጤና ባለሞያዎችን በከፍተኛ የሕክምና ትምህርት ተቋሞቿ በማስተማር እንደ ቀጣናዊ የልህቀት ማዕከል እያገለገለች ትገኛለች ብለዋል።
በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለ ራዕይ መሪነት ሀገሪቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉሪቱ መሪ ለመሆን ራሷን እያዘጋጀች መሆኑን አመልክተዋል።
በአፍሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች እና የኢንዱስትሪው ዘርፍ በጋራ ሊሠሩ፣ የምርምር ውጤቶችም የፖሊሲ መመሪያ በመሆን የሕዝቡን ሕይወት በተግባር ሊለውጡ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
በጋራ በማስተማር፣ ፈጠራን በማምጣትና በጋራ በመምራት እውቀት ሰብዓዊነትን የሚያገለግልባትን ጤናማ አፍሪካን መገንባት እንደሚቻልም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።