ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ የሚተርፍና ለተለዋዋጭ የጤና ሁኔታዎች የተዘጋጀ የሰው ኃይል እየገነባች ነው - ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ የሚተርፍና ለተለዋዋጭ የጤና ሁኔታዎች የተዘጋጀ የሰው ኃይል እየገነባች ነው - ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ የሚተርፍና ለተለዋዋጭ የጤና ሁኔታዎች የተዘጋጀ የሰው ኃይል እየገነባች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
ለሦስት ቀናት የሚቆየውና ከ46 ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች የታደሙበት የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ጉባኤ 2026 በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ አፍሪካ ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎትን ለማረጋገጥና ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሚገባ የሰለጠነ፣ ብቁና ለወደፊቱ ዝግጁ የሆነ የጤና ባለሙያ ያስፈልጋታል ብለዋል።
ኢትዮጵያም ፍትሐዊ፣ ጠንካራና ሰው ተኮር የሆነ የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ሥርዓት የዛሬውን ፍላጎት ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ለነገውም ተግዳሮት የተዘጋጀ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ሽግግር የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጥበቃን በማጠናከር፣ የዲጂታል ሽግግርን በማፋጠን፣ የሀገር ውስጥ መድኃኒትና ሕክምና መሣሪያዎች ማምረትን በማሳደግ እንዲሁም ብቁና ለወደፊቱ ዝግጁ የሆነ የጤና ባለሙያ በማፍራት ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ጥራት ያለው አገልግሎትን ለእያንዳንዱ ዜጋ ተደራሽ እና ተመጣጣኝ የማድረግ ጠንካራ ግብ አለው ነው ያሉት።
ለዚህም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጥበቃ ለጤና ሥርዓቱ መሠረትና ለጉዞው ደጋፊ ምሰሶ ሆኖ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ሀገሪቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ በጤና መሠረተ ልማት እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ወደ ማኅበረሰቡ በማቅረብ አስደናቂ ስኬቶችን ማስመዝገቧንም ጠቅሰዋል።
በዲጂታል ሽግግር በኩልም ቴክኖሎጂ ሰዎችን የሚያገለግልበትና ፈጠራ ሕይወትን የሚያሻሽልበት ሥርዓት ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና የጤና ተቋማት የዲጂታል ምዝገባ ከ52 ሺህ በላይ ተቋማትን እርስ በርስ ማስተሳሰር መቻሉን ገልጸዋል።
የኮቪድ ወረርሽኝን ጨምሮ የቅርብ ጊዜዎቹ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የጤና አደጋዎች እንዲሁም የአህጉሪቱ ተግዳሮቶች ጠንካራ የሀገር ውስጥ የክትባትና የመድኃኒት ማምረቻ ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ማሳየታቸውንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ማምረቻዎች ስትራቴጂካዊ ትኩረት መስጠቷንም ሚኒስትሯ ጨምረው ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ በአሁኑ ወቅት ከ63 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ እየሆነበት ያለውን በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓት በማስፋፋት፣ ማኅበራዊ የጤና መድህንን በማሳደግና የሀገር ውስጥ ሀብትን በማሰባሰብ ዘላቂ የጤና ፋይናንስን የማጠናከር ሥራ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
የጤና የትኩረት መስኮች ስኬት የሚወሰነው ባለው ብቁ የሰው ኃይል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ለባለሙያዎች ልማት ቀዳሚ አጀንዳ መስጠቷን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በየዓመቱ ከ21 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችን እያስመረቀች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ አቅም ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ጭምር የሚተርፍ መሆኑን በመጥቀስ በቅርቡ ከአህጉሪቱ የመጡ ከ600 በላይ የሕክምና ተማሪዎች በስፔሻሊቲና በሰብ-ስፔሻሊቲ ሕክምና መሰልጠናቸውን አውስተዋል።
በመጨረሻም፣ የባለሙያዎችን ትምህርት በማጠናከርና ለተለዋዋጭ ፍላጎቶች የተዘጋጀ አቅም በመፍጠር ረገድ በአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ስብስብ ሊጫወት የሚገባው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።