ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና ዲጂታል የጤና ሥርዓት የአህጉሪቱ መሪ ለመሆን ራሷን እያዘጋጀች ትገኛለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና ዲጂታል የጤና ሥርዓት የአህጉሪቱ መሪ ለመሆን ራሷን እያዘጋጀች ትገኛለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ለሦስት ቀናት የሚቆየውና ከ46 ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች የታደሙበት የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ጉባኤ (MedEDAfrica 2026) በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምርምርና በአጋርነት ዙሪያ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች የአፍሪካን ሕዝብ የወደፊት ጤና እና ደኅንነት የሚወስኑ ናቸው ብለዋል።


 

በአሁኑ ወቅት አህጉሪቱ ወረርሽኞች፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ ስደት እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በጤና ሥርዓቶቿ ላይ ከባድ ፈተና እየደቀኑባት ይገኛል ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ባለሙያዎች እጥረት፣ በቂ ያልሆነ የስልጠና መሠረተ ልማት እና የተማሩ ባለሙያዎች ፍልሰትም አሁንም ድረስ የሚፈትኑ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሆኖም አፍሪካ መቼም ቢሆን በፈተናዎቿ ተሸንፋ እንደማታውቅ ገልጸው ሁልጊዜም በጽናቷ፣ በፈጠራ ብቃቷ እና የተሻለ መጻኢ ጊዜን ለመገንባት ባላት ቁርጠኝነት እንደምትታወቅ ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ የአፍሪካ ወጣት ኃይል የአህጉሪቱን የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስፈልገውን እውቀት፣ ክህሎት እና ዕሴቶች የታጠቀ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ በማስገንዘብ፥ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት በቁርጠኝነት እየሠራችበት ትገኛለች ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ትምህርት ማስፋፋት፣ አዳዲስ የሕክምና ትምህርት ተቋማትን መገንባት፣ ነባር ተቋማትን ማጠናከር እንዲሁም ወጣት ኢትዮጵያውያን በጤና ሳይንስ ዘርፍ ሙያ እንዲሰማሩ ሰፊ ዕድሎችን መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከዚህም ባለፈ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ባለሙያዎችን በማስተማር ቀጣናዊ የስልጠና ማዕከል መሆን መቻሏን ጠቁመዋል።

ሆኖም ተደራሽነትን ከማስፋፋት ባለፈ በቀጣይ የላቀ ጥራትና ብቃት ማረጋገጥ የሀገሪቱ ዋና ግብ መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉሪቱ መሪ ለመሆን ራሷን እያዘጋጀች ትገኛለች።

ለዚህም በጤና ኢንፎርማቲክስ፣ በዲጂታል ጤና፣ በውስብስብና የረቀቀ ሕክምና፣ በሮቦቲክስ እና በኤአይ የታገዘ የበሽታ ምርመራ ላይ ትኩረቱን ያደረገውን የመጀመሪያውን የኤአይ ዩኒቨርሲቲ ለመመረቅ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መደረሱን ይፋ አድርገዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት በበሽታ ምርመራ፣ የወረርሽኞችን መከሰት አስቀድሞ በመጠቆም፣ ሕክምናን እንደየሰው ሁኔታ በማዘጋጀት ረገድ አብዮት እየፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።

አፍሪካ በዚህ የዘመኑ ሽግግር ውስጥ ተመልካች ብቻ ሳትሆን የራሷ የፈጠራ ባለቤት፣ አምራች እና መሪ መሆን እንዳለባትም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሕክምና ትምህርት ተቋማት በየጊዜው አዳዲስና ሕይወት አድን የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በሥርዓተ ትምህርቶቻቸው ውስጥ ማካተት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ለዚህም በአካዳሚው፣ በኢንዱስትሪው እና በክሊኒካዊ አሠራር መካከል ያለውን ሰንሰለት ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ስብስብ የአፍሪካን የጤና ባለሙያ ኃይል ለማጠናከር እና የአጀንዳ 2063 አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም