ቀጥታ፡

ያለፉት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 29/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በጉሩሞ ላዲሳ ቀበሌ ተካሂዷል።

በወቅቱም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ሥራዎች የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ያስቻሉ ናቸው።


 

በመርሃ ግብሩ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ የመሬት ለምነት እንዲጠበቅና የውሃ አካላት አቅማቸው እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው፣ ይህም በግብርናው ዘርፍ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አስታውቀዋል።

ዘንድሮ በሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በከተማው የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር የሚጠብቁና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አበርክቶ ያላቸው ችግኞች በስፋት እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

በዚህም ለደን፣ ለጥላ፣ ለውበት፣ ለኢኮኖሚ ምንጭነት የሚውሉ እንደ ቡና፣ ፍራፍሬ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው የችግኝ ዓይነቶች ትኩረት በመስጠት የመትከል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሕዝቡ ዘንድ እየዳበረ የመጣው ችግኝ የመትከል ባህል እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፣ የተተከሉትን ችግኞች በመጠበቅና በመንከባከብ ለውጤት እንዲበቁ የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት ይጠናከራል ብለዋል።


 

የከተማው ግብርና መምሪያ ኃላፊ ንጋቱ ቡሹራ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የቡና፣ የእንሰት፣ የፍራፍሬና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ መጀመሩን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩም 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል 680 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን አስታውቀዋል።


 

ችግኝ መትከል ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር መስተካከል የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ በየዓመቱ ችግኝ እየተከሉ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ካሳሁን ሎሃ እና አርሶ አደር ኢዮብ ሰማ ናቸው።


 

ችግኝ መትከል ከጀመሩ ወዲህ የተራቆቱ አካባቢዎች ለምተው ምርት መስጠት በመጀመራቸው፣ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የደረሱ ፍራፍሬዎችን ሸጠው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ለማስቀጠልም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበር ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ወደ ሥራ መግባታቸውን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም