ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ለሰላም ያላቸውን ሚና ማጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን በሥራዎቻቸው ለሀገር ሰላም ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መገናኛ ብዙኃን ሊጫወቱት የሚችሉትን ሚና አስመልክቶ ለሚዲያ ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።

በስልጠናው መክፈቻ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፣ መገናኛ ብዙኃን ለሰላም ያላቸውን ሚና ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ለሀገራዊ መግባባት መፈጠርና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ተግባቦት (ኮሙኒኬሽን) ወሳኝና ቁልፍ መሣሪያ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

የሚዲያ የመረጃ ተደራሽነት ሥራ የሰውን ልጅ የማዳን ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃን በማሰራጨት የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በበጎ መንገድ የመምራት ሰፊ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙኃን የሰላም አርበኞችን የሚፈጥሩበት ጊዜው አሁን ሲሉም ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ጨምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን የሚሰሯቸው ዘገባዎች ለሰላም ግንባታ የሚበጁና ለሀገር ዕድገት አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ ሊሆን እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።

መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የኅብረተሰቡን አንድነት እና አብሮ የመኖር እሴት የሚያጎለብቱና ብዝኃነትን በሕዝቡ ዘንድ የሚያሰርጹ ሊሆኑ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም