ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የቅርስ ሃብቶች በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ የሚሻገር አስደናቂ ሥራ ሰርቷል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የታሪክ፣ የተፈጥሮና ባህላዊ የቅርስ ሃብቶች በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ የሚሻገር አስደናቂ ሥራ መስራቱን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለምአቀፍ ተቋማት መሪዎች ከፍተኛ የዲፕሎማቶች ልዑክ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጉብኝት አድርገዋል።


 

የዲፕሎማቲክ ልዑካን የላሊበላ ጉብኝት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዕምቅ አቅም ለዓለም ለማስተዋወቅና በቅርስ ጥበቃ የሚደረገውን ዓለምአቀፍ ድጋፍ ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የአስደናቂ ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ናት።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኒስኮ) የተመዘገበው የላሊባላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኪነ-ሕንፃ የአሰራር ጥበብ ዓለምን ያስደመመ ድንቅ የጥበብ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የላሊበላን ቅርስም ለኃይማኖታዊ ሥርዓትና ዓለምአቀፍ ጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር የዘላቂ ቅርስ ጥበቃ መሠረተ ልማት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኪነ-ሕንፃ ጥበብ ከመጠበቅ ባሻገርም የአብያተ ክርስቲያናቱን የካበቱና ውድ የሥነ-ጽሑፍ ሃብቶች ዲጂታላይዝ በማድረግ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ሃብቶች ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማልማት የሰጡት ትኩረት የቅርስ ጥበቃ ውጤታማነትን አሳድጓል ብለዋል።

የጎንደር አፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጅማ አባጅፋር ቤተ-መንግሥት ዕድሳት የመደመር መንግሥት ድንቅ ሥራ አብነቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።


 

የዘላቂ ቅርስ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኃላፊ ኪዳነማርያም ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ በላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት ሥር ሰፋፊ መሠረተ ልማትቶች መካተታቸውን አረጋግጠዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክትም ቅርሱን ጠብቆ ለቀጣዩ ትወልድ ለማሻገር ትልቅ ዕድል መሆኑንና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን አባላት የላሊበላ ጉብኝት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ማንሰራራት የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ደግሞ የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሳይ ወዳጆ ናቸው።

የመደመር መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠው ትኩረት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ በመጠበቅ፣ በማልማትና በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም