በአስተዳደሩ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ በመፍታት በኩል ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ በመፍታት በኩል ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል
ድሬዳዋ፤ ሰኔ 29/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተቀናጀ አሰራር በመመለስ በኩል ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።
ከንቲባ ከድር ጁሃር የአስተዳደሩን የአስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የ2018 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በሪፖርታቸው እንደገለፁትም፤ የአስተዳደሩን ነዋሪዎች መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት በትኩረት ተሰርቷል።
ዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለስ አኳያ ተጨባጭ ውጤቶች የተገኙባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።
በተለይ ህብረተሰቡን ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የተከናወኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ የአነስተኛ መስኖና የውሃ ፕሮጀክቶች የገጠሩን ህብረተሰብ ጥያቄዎች በተጨባጭ የመለሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል እየተሰጡ የሚገኙ ፈጣን አገልግሎቶች የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት ማስቻላቸውንም ነው የተናገሩት።
በኮሪደር ልማት የተከናወኑት የተቀናጁ ልማቶችም ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጋት ይገኛል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት በኢንቨስትመት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የከተማዋን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከልነት እያረጋገጡ መሆናቸውንም አንስተው እነዚህን ውጤታማና ተጨባጭ ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ የማድረሱ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባዔው ከንቲባው ባቀረቡት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያይቶ ሪፖርቱን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባዔው ከሪፖርቱ በተጨማሪ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማትን የዕቅድ አፈፃፃምና የድሬዳዋ አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅም ይጠበቃል።