ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ተረከበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አቤል ሀብታሙ በ70ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ጎሉን አስቆጥሯል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ54 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና በ68 ነጥብ ዓመቱን ጨርሷል።

ጨዋታውን ተከትሎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ የሆነው ሲዳማ ቡና ዋንጫውን ተረክቧል።

የሊጉ ዋንጫ ሲዳማ ቡና በ1999 ዓ.ም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ያሳካው ትልቁ ድሉ ነው።

ሻምፒዮንነቱን ተከትሎ  በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።

ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ዋንጫውን ለማንሳት ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ይፋለማል።

በዋንጫ ስነ ስርዓቱ ላይ በርካታ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ታድመዋል።

በተጨማሪም ሲዳማ ቡና ዛሬ የተጠናቀቀውን ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በማጠቃለያ መርሐ ግብር ወላይታ ድቻን በመለያ ምት በመርታት ዋንጫውን አንስቷል። በዚህም ድርብ ድል አሳክቷል።

በሊጉ የመዝጊያ ስነ ስርዓት የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የዘንድሮው የሊጉ ውድድር ዛሬ በ38ኛ ሳምንት ተቋጭቷል።

ምድረ ገነት ሽሬ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ መቀሌ 70 እንደርታና አርባምንጭ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረዱ ክለቦች ናቸው።

ከከፍተኛ ሊግ ያደጉት ሃላባ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በሊጉ ይሳተፋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ናትናኤል ዳንኤል እና የፋሲል ከነማው ታምራት እያሱ በተመሳሳይ 15 ጎሎች በጋራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቀዋል።

የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው በ14 ግቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም