ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ጎንደር ፤ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ አካሄዷል።


 

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው። 

ለአብነትም  በበጀት ዓመቱ በባህር ዳርና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ከ266 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የገበያ ማዕከላት  ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የገበያ ማዕከላቱም ተደራጅተውና በግል የሙያ ዘርፎች የስራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ሴቶች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የማዕከላቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም ለ100 ሴቶች ቋሚ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲያገኙ ዕድልን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የሴቶችንና የህጻናትን መብት በማስጠበቅና በሌሎች ተያያዥ ተግባራት የተጀመሩ ስራዎች በአዲሱ በጀት ዓመት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድጎ በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ ለ33 ሺህ ሴቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ገልጸዋል። 


 

በተጨማሪም ሰባት የህፃናት ማቆያዎችን በማስገንባት የሚያጠቡ እናቶች ልጆቻቸውን በቅርበት እየተከታተሉ መደበኛ ስራቸውን በትጋት እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎትም አቅመ ደካሞችን፣ ህጻናትን፣ የአካል ጉዳተኞችንና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመደገፍ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።

"ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ከሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ነጻ የሆኑ 25 ቀበሌዎች ተፈጥረዋል" ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉቀን ጌታሁን ናቸው። 

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በተለያየ ምክንያት ለተቸገሩ 64 ሴቶች ከክልሉ በተገኘ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የማቋቋም ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በዕለቱም በጎንደር ከተማ የተገነባውን የሴቶችና ህጻናት የተሃድሶ ማዕከል ወደ ስራ የማስገባት ተግባር ተከናውኗል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም