ተመራቂ እጩ መምህራን በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ሙያዊ ሃላፊነት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ እጩ መምህራን በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ሙያዊ ሃላፊነት አለባቸው
ሰቆጣ ፤ሰኔ 28/2018(ኢዜአ)፡- ተመራቂ እጩ መምህራን በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ሙያዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ ገለፁ።
የሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ በዲግሪና በዲፕሎማ ደረጃ ያስተማራቸውን 484 እጩ መምህራንን በዛሬው እለት አስመርቋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ በወቅቱ፤ ሀገራችን ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ የትምህርት ዘርፉ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
ተተኪው ትውልድ የተማረና በፈጠራ ክህሎት የዳበረ እውቀት እንዲገነባ ለማስቻል መምህራን ያላቸው ድርሻም የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ተመራቂ እጩ መምህራን ሀገር አሻጋሪና በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ሙያዊ ሃላፊነት አለባችሁ ብለዋል።
የሰቆጣ መምህራን ኮሌጅ ዲን ወርቁ ጌጡ እንዳሉት ኬሌጁ ዕጩ መምህራንን በመደበኛና በክረምት መርሃ ግብሮች በማስተማር ለትምህርት ስርዓቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዘንድሮው ዓመትም በዲግሪና በዲፕሎማ ደረጃ ያስተማራቸውን 484 እጩ መምህራንን በዛሬው እለት ማስመረቁን አስረድተዋል።
በዛሬው እለት ካስመረቃቸው መካከል ኮሌጁ ለመጀመሪያ ጊዜ በኽምጣኟ ቋንቋ በዲግሪ መርሃግብር ያስተማራቸው ዕጩ መምህራን ይገኙበታል ብለዋል።
ዕጩ መምህራን የተማረ ዜጋ ለመቅረፅና በፈጠራ የበለፀገ ትውልድ እንዲፈጠር የሙያ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዲግሪ መርሃ ግብር ተመራቂ ዕጩ መምህር ወርቄ ደሳለኝ እንዳሉት በኮሌጁ ባገኙት እውቀት በራስ የሚተማመን የተማረ ዜጋ ለመፍጠር ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ዕጩ መምህር ኪሮስ ተክሌ በበኩላቸው በተማሩት የመምህርነት ሙያ በፈጠራ የበለፀገና የተማረ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ርብርብ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።