በክልሉ በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
ሆሳዕና ፤ ሰኔ 28/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ 2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ትምሀርት ቢሮ ገለፀ።
በክልሉ የትምህርት ሴክተር የ 2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2019 የቅድመ ዝግጅትና የክረምት ስራዎች ዙሪያ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በ 2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ።
የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል እና ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት ትኩረት ተደርጎ ሲመራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
ማህበረሰቡን በማሳተፍ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ማድረግ፣ የትምህርት ቤቶችን ጀረጃ ማሻሻል፣ የትምህርት ግብዓት ማሟላትና መሰል ተግባር በስፋት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ደግሞ ለአብነት አንስተዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት ስለማምጣታቸው አንስተው፤ ስራዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የትምህርት አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም ነው ያስገዘቡት።
በመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም፤ በዞኑ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ612 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ ሲተገበር ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም የበርካታ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ስለመቻሉ አንስተው፤ በዘርፉ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ስኬት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የሀድያ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ዴታሞ ጡምደዶ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ የቆዩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ በ 80 ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብር በማካሄድ የመጠነ ማቋረጥ ችግር የመቅረፍና ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለፁት።