ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የምገባ ማዕከላት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 28/ 2018(ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የምገባ ማዕከላት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ሲሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 30ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የምገባ ማዕከላት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

አስተዳደሩ የነዋሪዎችን ሕይወት ለመለወጥና ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር በርካታ ሰው-ተኮር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወቅታዊ ችግሮቻችንን በጋራ እየተሻገርን ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን ብለዋል።

ይህ አዲስ የተመረቀው ማዕከል ከቂርቆስ፣ ከሸራተን ማስፋፊያ እና ከካሳንቺስ አካባቢ ተነስተው በአራብሳ አካባቢ ቤት ተሠርቶላቸው የገቡ አረጋውያን እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ነዋሪዎች የተገነባ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ የነዋሪዎችን ጊዜያዊ የችግር ሸክም ከመቅረፍ ባለፈ በዘላቂነት ቋሚ የሥራ ዕድል ማግኘት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ የተጀመረበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለወገኖቻችን ይሄንን ስናቀርብ እኛ ከመመገብ ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠር ለዜጎቻችን ያለንን ክብርና ፍቅር የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ጊዜያዊ የኑሮ ችግሮችን በዚህ መልክ እየተደጋገፉ በማለፍ በዘላቂነት ግን ሀገርን ለማበልጸግ ሌት ተቀን ጠንክረን እየሰራን ነው ብለዋል።


 

ማዕከሉ እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ባለሀብቶችና አጋር አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የለሚኩራ የክፍለ ከተማ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ልመንህ ምህረቱ በበኩላቸው፥ ማዕከሉ በውስጡ ሰፊ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ ክፍል፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና የሠራተኞች ክፍል፣ የምግብ መጋዘን እና 10 ክፍሎች ያሉት መታጠቢያ ክፍልን ያካተተ መሆኑ ገልፀዋል።

ይህ ግዙፍ የምገባ ማዕከል ሙሉ በሙሉ በክፍለ ከተማው በሚኖሩ ባለሀብቶች እና በጎ ፈቃደኞች ትብብርና ድጋፍ የተገነባ መሆኑም ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የማዕከሉ ተጠቃሚ የሆኑ አረጋውያንና ነዋሪዎች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም