ባገኘነው ዕውቀት ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ዕይታን በመጠቀም ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ባገኘነው ዕውቀት ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ዕይታን በመጠቀም ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 28 /2018(ኢዜአ) ፦ያገኘነው ዕውቀት ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ዕይታን በተሻለ መንገድ እንድንረዳው አድርጎናል፤ ይህን ተጠቅመን ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ተመራቂዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በመከላከያና ስትራቴጂክ የደህንነት ጥናት መስክ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን ተመራቂዎች አስመርቋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች እንደገለጹት፤ በኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ የተሰጣቸው ሥልጠና ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ዕይታን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል የኢፌዴሪ አየር ኃይል የ3ኛ አየር ምደብ ምክትል አዛዥ እና የተዋጊ ሄሊኮፕተር አብራሪና አስተማሪ ኮሎኔል ደረስ እንዳለ እንደገለጹት፤ በኮሌጁ ያካበቱት እውቀት ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በግልጽ ለመረዳትና ለመተንተን የሚያስችል ከፍተኛ አቅም ፈጥሮላቸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታ በውል ለመረዳት ማስቻሉን ገልጸው፤ ይህንን ስትራቴጂካዊ ዕይታ መሠረት በማድረግ ሀገራቸው የምትሰንቀውን ታላቅ ህልምና ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት ለመስራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት ከመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ሌተናል ኮሎኔል ዶክተር ቴዎድሮስ ገብረ ሩፋኤል በበኩላቸው፤ በስትራቴጂክና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ የተከታተሉት ትምህርት ዘርፈ-ብዙ ሁኔታዎችን በጥልቀት ለመተንተን ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የበዙበት መሆኑን አመልክተው፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ በጎ ውጤት እንደሚያስገኙ አመልክተዋል።
ሌላው ሰልጣኝ ከአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የመጡት አቶ ጌታሰው ደሴ እንዳሉት፤ ሥልጠናው ለሀገር አንድነት፣ ለሀገር ፋይዳ እና ለተቋማት ግንባታ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋጽኦ ለማበርከት ትልቅ አቅምና ወደፊት ለሚሰማሩበት የሥራ መስክም ስንቅ እንደሆናቸው ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ከልዩ ዘመቻዎች እዝ የመጡት ሌተናል ኮሎኔል ደረጀ ዳባሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ያገኙት ዕውቀት የእለት ተእለት ተግባራቸውና ከሙያቸው ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ስትራቴጂካዊ አካባቢውን፣ ጂኦፖለቲካውን እና አጠቃላይ ሁኔታውን በተገቢው መንገድ ለመረዳት አስችሏቸዋል።
ትምህርቱ ለተግባራዊ ስራቸው ጠንካራ መነሻ ከመሆኑም በላይ፣ ባላቸው የረጅም ጊዜ ልምድ ላይ ትልቅ አቅም የገነባ መሆኑንም አክለዋል።
የኮሌጁ ሰልጣኝ የሆኑት ኮሎኔል እማምር አያሌው በበኩላቸው፤ ቀጣናዊና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ በደንብ በመረዳት መተንተን የሚችል ጠንካራ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአስተሳሰብ የበሰለ፣ በስትራቴጂካዊ እውቀት የዳበረና ለማንኛውም ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ሠራዊት መገንባቱን ጠቁመዋል፡፡