የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች በጥናት ላይ ተመስርቶ በፍጥነት ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቷል-አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች በጥናት ላይ ተመስርቶ በፍጥነት ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቷል-አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)
ደሴ፤ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በቀጣዮቹ ዘጠና ቀናት የሕዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በጥናት ላይ ተመስርቶ በፍጥነት ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
በዘጠና ቀናት ዕቅድና አፈጻጸም ላይ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በደሴ ከተማ ውይይት እያካሄዱ ነው።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የክልሉን ዕድገትና የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ አመራር በመስጠት በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
በክልሉ በቀጣዮቹ ዘጠና ቀናት የሕዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በጥናት ላይ ተመስርቶ በፍጥነት ለመመለስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በዚህም የክረምት ሥራዎችን ጨምሮ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች ላይ በመረባረብ፣ የተጀመረውን ዕድገትና ብልፅግና ዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አክለዋል።
በተለይም በየደረጃው ያለው አመራር የመረጠውን ሕዝብ በላቀ ሁኔታ ለማገልገልና ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ለዚህም የመንግሥትን አፈጻጸም በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ፣የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት፣ የዜጎችን ገቢ ማላቅና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት ላይ በማተኮር ችግሮችን የመፍታት አቅጣጫ መከተል እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
የክልሉን ሰላም ለማጽናት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ተግባር መከናወኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በቀጣይም ሰላሙን በዘላቂነት በመጠበቅ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩም ላይ የክልል፣የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።