የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃና ለስነ-ምህዳር መታደስ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃና ለስነ-ምህዳር መታደስ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 28/ 2018 (ኢዜአ):-የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ ለአካባቢ ጥበቃና ለስነ-ምህዳር መታደስ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በዚህም ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ እስከ አሁን ባሉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ የደን፣ የፍራፍሬና የጥላ ችግኞችን ማልማት ተችሏል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡
በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሒዷል፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አካባቢን ከብክለትና መራቆት የምንጠብቅበት አንዱ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም ለዓለም የአየር ንብረት መጠበቅ በረከት እየሆነ መምጣቱን ተናግረው፤ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድም ሚና እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ ለአካባቢ ጥበቃና ለስነ-ምህዳር መታደስ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ በረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ አካባቢ በአሁኑ ወቅት በተሰራ የመልሶ ልማት ስራ ከአደጋ ስጋት ወደ ሀብትነት እየተቀየረ መጥቷል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገዛኸኝ ዴሲሳ በበኩላቸው፤ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ በአሁኑ ወቅት በችግኝ እየተሸፈነ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም በአሁኑ ወቅት በመልሶ መጠቀም ወደ ሀብትነት እየተቀየረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች፤ አረንጓዴ አሻራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የነበሩ የቆሻሻ መጣያ መሬቶች አሁን ላይ መልሰው በማገገም በአረንጓዴ ተክሎች መሸፈናቸውን ተናግረዋል።