ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና የዋንጫ ሽልማቱን በሚረከብበት ዕለት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና የዋንጫ ሽልማቱን በሚረከብበት ዕለት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና በ68 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ51 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ሲዳማ ቡና የሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱን ያረጋገጠው በ36ኛ ሳምንት ከነገሌ አርሲ ጋር አንድ አቻ መለያይቱን ተከትሎ ነው።
በ1999 ዓ.ም የተመሰረተው ሲዳማ ቡና የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ባለቤት መሆኑ በ19 ዓመት የክለቡ ጉዞ ውስጥ ትልቁ የሚባለው ስኬቱ ነው።
ለረጅም ሳምንታት የሊጉ አናት ላይ የቆየው እና በአንጻራዊነት ወጥ አቋም ያሳየው ሲዳማ ቡና ከዛሬው ጨዋታ በኋላ ታሪካዊውን ዋንጫ የሚረከብ ይሆናል።
የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የዋንጫ አቀባበል ድባቡን ይበልጥ ለቡድኑ ያደምቀዋል።
ቡድኑ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት ይሳተፋል።
በተጨማሪም ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚፋለም ይሆናል። ዓመቱን በሁለት ዋንጫ የማጠናቀቅ እድል አለው።
በ37ኛ ሳምንት ከሃዋሳ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዓመቱን በድል ለመደምደም ከሻምፒዮኑ ጋር ይፋለማል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቅቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።
በዝናብ ስጋት ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ የተዛወረው የሲዳማ ቡና እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ የ2018 ዓ.ም የሊጉ መዝጊያ ጨዋታ እሁድ ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በሳምንቱ አጋማሽ ማስታወቁ ይታወሳል።