ለውይይት የቀረቡት አጀንዳዎች ዘመናትን ለተሻገሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔን በመስጠት የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ የሚወስኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለውይይት የቀረቡት አጀንዳዎች ዘመናትን ለተሻገሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔን በመስጠት የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ የሚወስኑ ናቸው
ሀዋሳ፤ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለምክክር ጉባኤው ያዘጋጃቸው ስምንቱ አጀንዳዎች፣ ዘመናትን ለተሻገሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔን በመስጠት የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ የሚወስኑ መሆናቸውን የሲዳማ ክልል ወጣቶች ማህበር ገለጸ።
ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት አሳታፊ በሆነ መንገድ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች መነሻ በማድረግ፣ ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሄደው ዋና የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ ስምንት አጀንዳዎችን ለይቶ አቅርቧል፡፡
በጉባኤው አጀንዳዎች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገው የሲዳማ ክልል ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት በቃሉ መሰረት፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት አሳታፊ በሆነ መልኩ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ ማከናወኑን ገልጿል።
ሂደቱ በርካታ ምዕራፎችን አልፎ ለዚህ መብቃቱን ያደነቀው ወጣት በቃሉ፣ ለዋናው የምክክር ጉባኤ የተለዩት አጀንዳዎች ዘመናትን ለተሻገሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ የሚወስኑ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በአጀንዳዎቹ ላይ በጥልቀት በመወያየት ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔን መሻት እንደሚገባ ጠቅሶ፣ ይህንን ወርቃማ ዕድል ማባከን እንደማይገባና ሂደቱ ፍሬያማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን እንዲወጣም አሳስቧል፡፡
የማህበሩ አባል የሆነችው ወጣት በረከት ጴጥሮስ በበኩሏ፤ የሀገርን ልማትና ሰላም ለማስቀጠል ልዩነቶችን በውይይትና በንግግር መፍታት ወቅቱ የሚጠይቀው የሰለጠነ መንገድ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩነት የፈጠሩና የግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያዘጋጃቸው አጀንዳዎች ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡና ጠንካራ ሀገርን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጻለች፡፡
እንደ ሀገር የተፈጠሩ ልዩነቶችንና ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በምክክር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ዕድል መሆኑን የገለጸው ደግሞ የክልሉ ወጣቶች ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ወጣት አሸናፊ ኤፍሬም ነው፡፡
ኮሚሽኑ ለምክክር ጉባኤው የለያቸው አጀንዳዎች ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡና የበለጸገች ሀገርን ለትውልድ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
ኮሚሽኑ ከዋናው ጉባኤ በፊት በየደረጃው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሲያደርግ የነበረው ውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ የመነጋገር ባህልን ማሳደጉን የጠቀሰው ወጣት አሸናፊ፣ ምክክሩ የታለመለትን ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪውን አስተላልፏል።