ቀጥታ፡

የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018(ኢዜአ):- የክልሎች ቅኝት- በወፍ በረር

በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?

ኢትዮጵያ እያከናወነች ነው

የገጠር ትራንስፎርሜሽን

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የከተሞች ኮሪደር ልማት ወደ ገጠሩም ተስፋፍቶ የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗርና አመጋገብ እንዲሁም ጤናን መሰረት በማድረግ የገጠር ኮሪደር ልማት በመከናወን ላይ ይገኛል።


 

ለጤናም ይሁን ለኑሮ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ለዘመናት በተመሳሳይ ሁኔታ የኖረው አርሶና አርብቶ አደሩ አሁን ላይ መሰረታዊ የአኗኗር ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በገጠር የኮሪደር ልማት የሰዎችና እንስሳት መኖሪያ እየተለየ፤ በባዮ ጋዝ እና በፀሃይ ብርሃን በሚሰራ የሃይል ምንጭ መብራት ማግኘትና ምግብ መስራት የተቻለበት፤ በጓሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ የሚቻልበት ዘመናዊ አኗኗር ጀምረዋል።

የገጠር ትራንስፎርሜሽን የልማት እንቅስቃሴው በጅምር ላይ ቢሆንም በብዙ አካባቢዎች እየተስፋፋ ሞደል መንደሮች እየተበራከቱ መጥተዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ሀማሳ በ79 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ የተሰራው ሞዴል መንደር የዚሁ ጥረት ማሳያ ነው። 


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ለነዋሪዎች የተላለፈው የሀማሳ ሞዴል መንደር በአንድ ግቢ ውስጥ የንጽህና መጠበቂያ፣ የተደራጀ የቤት እንስሳት ማቆያ፣ በባዮ ጋዝ የሚሰራ የሃይል አቅርቦትን እንዲሁም የተሟላ የጓሮ ግብርናን ማእከል አድርጎ የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም መንግሥት በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ሞዴል ቤቶችን መስራቱን አስታውሰው ከዚህ በመነሳት ነዋሪዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት የራሳቸውን መኖሪያዎች መገንባት ጀምረዋል ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ''ንጽህና ካለ ጤና አለ፤ ምግብ ካለ ጤና አለ፤ የተስተካከለ ኮሪደር ካለ ሰላም አለ። እነዚህ ጉዳዮች ከፍተኛ ግምት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። የዜጎቻችንን ሕይወት ይቀይራሉ፤ የአኗኗር ዘዬአችንን ያሻሽላሉ፤ ኢትዮጵያን ወደ ምናስበው ከፍታ ወደ ምናስበው መሻሻል የመውሰድ አቅም አላቸው'' ሲሉም ተናግረዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ቀጥሎ በጋሞ ዞን የ'ዮ ሆልዲንግ’ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሀገር ለማስገባት እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ውጪ የሚደረግ መሆኑን አንስተዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ የከሰል ማምረቻ ፋብሪካዎች ተመርቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውንና ይህም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሙላት ባለፈ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እድል ይፈጥራል ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአርባምንጭ ዘመናዊ የኮንፈረንስ ሪዞርት መርቀው ስራ ያስጀመሩ ሲሆን በዶርዜ ሎጅ እና አካባቢው መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማን የኮሪደር ልማት፤ በከተማዋ የሚገኘውን ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓንም ጎብኝተዋል። በሁሉም ዘርፎች ኢትዮጵያ ማከናወኗን አጠናክራ ቀጥላለች፤ እድገትና ማንሰራራቷ ላይቀለበስ ጉዞውን ቀጥሏል።

ከዩኔስኮ ምርጥ አምስት ቅርሶች አንዱ

የቱሪዝም ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት እንዳስታወቀው የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለማችን ከፍተኛ ተጓዦች ከተመረጡ የዩኔስኮ ምርጥ አምስት ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኗል።


 

በዩሮኒውስ የዜና አውታር በተደረገ ጥናት፤ ሁሉንም የዓለም ክፍሎች ያዩ አንጋፋ ተጓዦች ካስቀመጧቸው ተወዳጅ የዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በግንባር ቀደምትነት ተቀምጧል። 

በዚሁ ሳምንትም ከአርባ በላይ ሀገራት እና ከአሥር በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተወከሉ ዲፕሎማቶች  የላሊበላ ከተማና ውቅር አብያተክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።


 

ይህ ከፍተኛ የዲፕሎማቶች ልዑክ በቆይታው ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን፣ የሕንጻ ጥበብ እና የኢንጂነሪንግ ጥበብ ማስተርፒስ እንዲሁም የሃይማኖትና የታሪክ ሕያው ምስክር የሆኑትን የዓለም ቅርስ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ አስተማማኝ መከታ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በመከላከያና ስትራቴጂክ የደህንነት ጥናት መስክ ያሰለጠናቸውን ተመራቂዎች በዚሁ ሳምንት አስመርቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ሰራዊቱ የውስጥ ባንዳና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ከንቱ ህልም በማምከን የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መልኩ እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄና ቀጣናዊ የትብብር መርህ ለማደናቀፍ ታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች ግንባር ፈጥረው እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ከባሕር ለማስወጣት የተጠቀሙበት የረጅም ዘመናት ሴራም ዛሬ ላይ “ፅምዶ” በሚል የተሰለፉ አካላት ስለመኖራቸው ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአደረጃጀት ልዩ እና በዘመናዊ ትጥቅ ተጠናክሮ በማንኛውም ሁኔታ ለሀገሩ ክብርና ሉአላዊነት መጠበቅ አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል። 

የ12ኛ ክፍል ፈተና

በሳምንቱ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ስኬታማ በሆነ መልኩ ተከናውኗል።


 

በሁሉም አካባቢዎች ተፈታኞች በበይነመረብ (ኦንላይን) እንዲሁም በወረቀት እንደየ ዝግጅቱና ምቹ ሁኔታውን መሰረት በማድረግ ፈተናውን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

በገጠር ኮሪደር አዲስ የህይወት ምእራፍ 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ በተገነባው ሞዴል የገጠር መንደር የሚኖሩ አርሶ አደሮች አዲስ የህይወት ምእራፍ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክና ሌሎች አገልግሎቶች የተሟላለት የገጠር ሞዴል መኖሪያ መንደር የአኗኗር ዘይቤያችንን ምቹና ዘመናዊ አድርጎታል ያሉት ነዋሪዎቹ ይህንን ላደረጉ ሁሉ እናመሰግናለን ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ የተገነባውን የገጠር ሞዴል መኖሪያ መንደር መመረቃቸው ይታወሳል፡፡

የግብርናና ገጠር ሽግግርን እውን በማድረግ የአርሶ አደሩን አኗኗር ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድን ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን አርሶ አደሩ በአቅራቢያው ማግኘት የሚያስችልና የኢኮኖሚ አቅሙን የሚያሳድጉ መሆናቸውን በወቅቱ ተናግረዋል።

በቀጣይም ተግባሩን በማስፋት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግን ፍልሰት ለማስቀረት በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ

በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ አኔ ዲማ ወረዳ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰኣዳ አብዱረህማንና የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም የአከባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተካሄዷል።


 

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን በወቅቱ፤ ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለትውልድ ቀጣይነት አስተማማኝ ዋስትና ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፤ በሸገር ከተማ የአካባቢውን አረንጓዴነት ለማረጋገጥና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።


 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 19 ነጥብ 1 ሚሊዮን የተለያዩ ዝርያ ያላቸውና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር ገብተናልም ብለዋል።

የባቡር መስመር ጥገና

የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥገናን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል።


 

የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በቅርቡ የጥገና ስራው የተጀመረውን የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት የጥገና ሂደት በዚሁ ሳምንት ጎብኝተዋል።

ከአዋሽ -ኮምቦልቻ -ሃራ ገበያ 392 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ፕሮጀክት በአራት አቅጣጫ የጥገና ሥራው እየተከናወነ መሆኑም ታውቋል።

ለልማት ተነሽዎች የተገነቡ ቤቶች

በዚሁ ሳምንት የጅማ ከተማ አስተዳደር ለልማት ተነሺዎች ያስገነባውን 300 መኖሪያ ቤቶች መርቆ ማስረከቡን እንመለከታለን።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ገመቹ፤ በክልሉ በገጠርም ይሁን በከተሞች ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የጅማ ከተማ ከንቲባ ጠሃ ቀመር፤ በከተማው በርካታ ፕሮጀክቶች በመንግስት እየተከናወኑ እንደሆኑና የተጠናቀቁትም ለአገልግሎት ክፍት እየተደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በከተማዋ በዚህ አመት 80 የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ጠቅሰው ዛሬ ለልማት ተነሺዎች ተገንብተው የተላለፉ መኖሪያ ቤቶች የዚሁ ጥረት አንድ አካል ናቸው ብለዋል።

እነዚህ መኖሪያ ቤቶች ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው ግንባታቸው ተጠናቆ ለ300 አባወራና እማወራዎች ተላልፈዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም