ቀጥታ፡

ብራዚል ከኖርዌይ፣ ሜክሲኮ ከእንግሊዝ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ ተጠባቂ ፍልሚያዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሁለት የ16 ውስጥ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ብራዚል ከኖርዌይ በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል 32 ውስጥ ጃፓንን 2 ለ 1 በመርታት ቀጣዩን ዙር ተቀላቅላለች።

ኖርዌይ ኮትዲቯርን 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ 16 ውስጥ ገብታለች።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጀችው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ኖርዌይ 2 ለ 1 አሸንፋለች።

ቶሬ አንድሬ ፍሎ እና ኬቲል ሬክዳል በወቅቱ ለኖርዌይ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ቤቤቶ የብራዚልን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ሀገራቱ ከ28 ዓመታት በኋላ በጥሎ ማለፍ መድረክ ተገናኝተዋል።

በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድኖቹ እርስ በእርሳቸው ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ኖርዌይ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናት በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ብራዚል ኖርዌይን እስከ አሁን አሸንፋ አታውቅም።

አምስት ግቦች በዓለም ዋንጫው ያስቆጠረው የኖርዌው አርሊን ሃላንድ እና አራት ግቦች ያለው ቪኒሸስ ጁኒየር በጨዋታው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

የሁለቱ ቡድኖች የፊት መስመር አቅም የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የጨዋታው አሸናፊ ከሜክሲኮ እና እንግሊዝ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።


 

በሌላኛው መርሐ ግብር ሜክሲኮ ከእንግሊዝ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በሜክሲኮ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከዓለም ዋንጫው አስተናጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሜክሲኮ በ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ኢኳዶርን 2 ለ 0 በመርታት 16 ውስጥ ገብታለች።

ተጋጣሚዋ እንግሊዝ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 2 ለ 1 በመርታት ወደ ሁለተኛው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

እንግሊዝ እ.አ.አ በ1966 ባዘጋጀችው ስምንተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ሰር ቦቢ ቻርልተን እና ሮጀር ሀንት ግቦቹን ለሶስቱ አናብስቶች በወቅቱ አስቆጥረዋል።

እንግሊዝ እስከ መጨረሻው በመጓዝ ብቸኛውን የዓለም ዋንጫ ክብሯን ተቀዳጅታለች።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከስድስት እስርት ዓመታት በኋላ ዳግም በዓለም ዋንጫው ተገናኝተዋል።

በዓለም ዋንጫው አምስት ጎሎች ያስቆጠረው የእንግሊዙ ሃሪ ኬን እና ሶስት ግቦች ያለው የሜክሲኮው ጁሊያን ኪኖኔስ በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም