የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ድል ማስመዝገብ ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ድል ማስመዝገብ ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 የፕሪፎንቴይን ክላሲክ -ዩጂን ዳይመንድ ሊግ እና በአሜሪካው የፒችትሪ የጎዳና ሩጫ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል።
በአሜሪካዋ ዩጂን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር፣ በሴቶች የሁለት ማይል ርቀት ብርቱ ፉክክር የተስተዋለበት ነበር።
ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው አትሌት አለሺኝ ባወቀ ስትሆን፣ የወቅቱ ፈጣን የሆነ ሰዓት 9:20.02 በማስመዝገብ በአንደኝነት አጠናቃለች።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሒሩት መሸሻ በ9:20.20 በሆነ ሰዓት በቅርብ ልዩነት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በዚሁ የሁለት ማይል ውድድር ላይ የተሳተፉት ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል።
አትሌት ማርታ አለማየሁ በ9:21.42 4ኛ ፣አትሌት የኔዋ ንብረት በ9:22.93 7ኛ እና አትሌት አሳየች አይቼው በ9:23.04 8ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች የአንድ ማይል ውድድር ላይ የተሳተፉት አትሌት ሳሮን በርሀ በ4:22.50 11ኛ ደረጃን እንዲሁም አትሌት ወርቅነሽ መሰለ በ4:36.80 13ኛ ደረጃን ይዘው ፈፅመዋል።
በሌላ በኩል 250ውን የአሜሪካ የነፃነት ቀን በዓል በማስመልከት በተካሄደው 57ኛው የፒችትሪ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ በአስደናቂ ሁኔታ ፍጥነት በመጨመር ውድድሩን በ31:02 በሆነ ሰዓት በአሸናፊነት አጠናቃለች።
ሌላኛዋ አትሌት መልክናት ውዱ በ31:03 በአንድ ሴኮንድ ተቀድማ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።