ቀጥታ፡

የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋታችን ተምረን ለልማትና ሰላም ግንባታ አርአያ በመሆን እየሰራን ነው-የቀድሞ ታጣቂዎች

ደብረ ብርሃን፤ሰኔ 28/ 2018(ኢዜአ)፡- የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋታችን ተምረን ለልማትና ለሰላም ግንባታ አርአያ በመሆን እየሰራን ነው ሲሉ የአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ህብረተሰቡን ተቀላቅለው በልማት ስራ ላይ የተሰማሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን የኢዜአ ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል።

ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል አጎላላና ጠራ ወረዳ የሚኖረው አወቀ ስለሺ፤ በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት ማህበረሰቡንም ይሁን ቤተሰቡን የጎዱበት አጋጣሚ ሲያስታውስ ከፍተኛ ጸጸት የሚሰማው መሆኑን ገልጿል።

በጫካ እንዲሰባሰቡ ያደረጓቸው አካላት ለዘረፋና ሃብት ማካበት የተሰለፉ መሆኑን በመረዳቱ የመንግስትን የሰላም ጥሪ መቀበሉን ተናግሯል።

ከስልጠና በኋላ በተደረገለት የገንዘብ ድጋፍና በተሰጠው የመስሪያ ቦታ ወደ ልማት በመግባት ከራሱም አልፎ ቤተሰቡንና ማህበረሰቡን የሚጠቅም ተግባር ላይ መሰማራቱን ገልጿል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋታችን ተምረን ለልማትና ለሰላም ግንባታ አርአያ በመሆን እየሰራን እንገኛለን፤ ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲል ተናግሯል።

በመሆኑም በጫካ የሚገኙ ወጣቶች ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከጥፋት በመውጣት የልማትና የሰላም አርአያ ለመሆን እንዲመጡ መልእክቱን አስተላልፏል።

ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ ሚኪያስ ቸርነት፤ በተሳሳተ መልኩ ወደ ጫካ በመግባት በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ በፈፀመው በደል መፀፀቱን ገልጿል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በተደረገለት ድጋፍ ወደ ልማት በመግባት ሰላማዊ ህይወት በመምራት ላይ መሆኑን ተናግሯል።

በጠመንጃ ትግል ከጥፋት በስተቀር የሚመጣ አንዳችም ውጤት የሌለ መሆኑን በመረዳት ሰላምና ልማትን በመምረጥ እየሰራ መሆኑን ገልፆ፤ ሌሎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችም ከተሳሳተ መንገዳቸው እንዲመለሱ አስገንዝቧል።

በሰሜን ሸዋ ዞን የአጎለላና ጠራ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አዳፍሬ ማንደፍሮ፤ የመንግስት የሰላም ጥሪ ብዙዎቹን ወደ ሰላማዊ ህይወት እየመለሳቸውና ሰርተውም እየተለወጡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በጫካ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂዎችም እየሄዱበት ያለው መንገድ የተሳሳተ እና ማህበረሰብን የሚጎዳ መሆኑን በመገንዘብ ጊዜ ሳያባክኑ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ መልእክት አስተላልፈዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ሃላፊ ዓባይ ዲሌ፤ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን የመቀበልና በዘላቂነት የማቋቋም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት የተመለሱት በተለያዩ የልማት መስኮች ተሰማርተው እየሰሩ ስኬታማ መሆናቸውን አንስተው፥ ሌሎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችም የእነርሱን ፈለግ በመከተል እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞንና አካባቢው ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በተለይም የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም