ቀጥታ፡

ሞሮኮ ካናዳን 3ለ0 በመርታት በዓለም ዋንጫው ሩብ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ መርሐ ግብር  ሞሮኮ ካናዳን 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በሂውስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የ26 ዓመቱ የአማካይ ተጫዋች አዜዲን ኡናሂ በ50ኛው ፤ በ82ኛው እና ሶፊያን ራሒሚ በጭማሪ ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥሯል።

የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድባትም በሁለተኛው 45 የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጋለች።

የሞሮኮው ወሳኝ ተጫዋች ኢስማኤል ሳይባሪ (አጥቂ)  ባጋጠመው የጡንቻ ጉዳት ምክንያት በ22ኛው ደቂቃ በሶፊያን ራሂሚ ተቀይሮ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሞሮኮ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪያ ሀገር ሆናለች። 

በሩብ ፍጻሜው ከፓራጓይ እና ፈረንሳይ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች። 

ኳታር እ.አ.አ በ2022 በተካሄደው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር በመሆን ታሪክ መስራቷ ይታወቃል።

የአትላስ አንበሶች በዘንድሮውም የዓለም ዋንጫ በስኬታማ ጉዟቸው ቀጥለዋል።

ከዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ካናዳ ጉዞዋ 16 ውስጥ ተገቷል። 

በሌላኛው የ16ቱ ጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ፓራጓይ ከፈረንሳይ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በፊላደልፊያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም