ቀጥታ፡

ሀዋሳ ከተማን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦የሀዋሳ ከተማን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት፣ የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሀብት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት፤ የሲዳማ ክልል የሀዋሳ ከተማን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ባለሀብቶች ወደ ሀዋሳ በመምጣት እውቀትና ሀብታቸውን ተጠቅመው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

ሀዋሳ መተላለፊያና ማረፊያ ከተማ በመሆኗ ባለሃብቶች በአካባቢው ያለውን ዕድል እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

ሀዋሳን በጋራ ለመገንባት የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው በቁርጠኝነት ለሰሩና የበኩላቸውን ሚና ለተወጡም ምስጋና አቅርበዋል። 

ሀዋሳ የደቡብ ፈርጥ፣ የሰላም ደሴት፣ ባላት ውብ ተፈጥሮ ምድረ ገነት የተባለች፣ እንዲሁም የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት የፍቅር ቤት ያስባላት ከተማ መሆኗን አንስተዋል። 

ሀዋሳን ለኑሮ፣ ለመዝናኛ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት የተመቸች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፣ የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሀብት ማሰባሰቢያ መድረክ የፕሮጀክት መገንቢያ ብቻ ሳይሆን፣ የነገንና አዲሱን ምዕራፍ በጋራ ለመገንባት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሀዋሳ በተፈጥሮ የታደለች ናት ያሉት ከንቲባው፤ ከተማዋን አልምቶ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የሀዋሳ ሐይቅ የቱሪዝም ምንጭና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አንስተው፤ የሐይቁን ዳርቻ ማልማት የከተማዋን ገጽታና ተስፋ የሚቀይር ታሪካዊ ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሀዋሳን ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ምቹ እንዲሁም ከተማዋን የአፍሪካ የቱሪዝምና የኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የፍቅር ሐይቅ፣ አሞራ ገደልና ዓሳ ገበያን ለነዋሪዎቿና ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ መታቀዱንም ተናግረዋል።

ከተማዋን በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት ለተወጠነው ፕሮጀክት ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ከዚህ መካከል ሁለት ቢሊዮን ብር ከከተማ አስተዳደሩ፣ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብሩን በገቢ ማሰባሰቢያ ለማግኘት መታቀዱን አስረድተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት በቀረበው ጥሪ መሰረት በመጀመሪያው ዙር የሀብት ማሰባሰቢያ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የዛሬው መድረክም የመጀመሪያ ዙር የሀብት ማሰባሰቢያ ማጠናቀቂያ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሀዋሳ ሐይቅን ለማልማት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም