ኢትዮጵያ የድህነትና ኋላቀርነት ታሪክን በሚሰብር የመነሳትና የብልፅግና የእጥፋት ዘመን ላይ ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የድህነትና ኋላቀርነት ታሪክን በሚሰብር የመነሳትና የብልፅግና የእጥፋት ዘመን ላይ ናት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የድህነትና ኋላቀርነት ታሪክን በሚሰብር የመነሳትና የብልፅግና የእጥፋት ዘመን ላይ ናት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሀብት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሀገራት ከችግርና ጉስቁልና የሚሻገሩበት የእጥፋት ጊዜ አለ።
ኢትዮጵያ ያለችበት ዘመን የእጥፋት፣ ብልፅግናና የመነሳት ዘመን መሆኑንም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በመንግስት መሪነት፣ በግል ባለሀብቱ ተሳትፎና ትብብር የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀዋሳ የልማት ፕሮጀክት ትልቅ በጀት የሚጠይቅ፤ ሲጠናቀቅም ለነገ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሁሉም አካባቢዎች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
አንድነታችንን እንደጋሻና ጦር በመጠቀም ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት የምናላቅቅበትና በጋራ የምናለማበት መጪው ጊዜ ብሩህ ነው ብለዋል።
መድረኩ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ በተመረጠበትና ለመንግስት ምስረታ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት መዘጋጀቱ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።